የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ሰልጣኞቹን አስመረቀ።

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ሰልጣኞቹን አስመረቀ።
****ነሀሴ 3/2018*****
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በደረጃ 6 (መጀመሪያ ዲግሪ) እና በደረጃ 7 (ሁለተኛ ዲግሪ) ያሰለጠናቸውን ወንድ 1499፣ ሴት 376፣ ብድምሩ 1875 ሰልጣኞች አስመርቋል።
ኢንስቲትዩቱ ከአገር ውስጥ ሰልጣኞች በተጨማሪ የደቡብ ሱዳን እና የሶማሌ ላንድ ዜጎችን አሰልጥኖ አስመርቋል።
በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
ኢትዮጵያ ያላትን ሀብትና ጸጋ በአግባቡ ተጠቅማ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል እንድትችል በዕውቀትና በተግባራዊ ክህሎት የተጠናከረ የሰው ኃይል መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና የሚያስፈልግ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ማጠናከር አስፈላጊ ነው፡፡
በመደመር መንግሥት የሰው ኃይል ልማትን ከሀገራዊ የምርታማነትና የኢንዱስትሪ ሽግግር ጋር በማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የሙያ ብቃት ያላቸው ዜጎችን ማፍራት እንደ ዋነኛ የልማት መሠረት መወሰዱን አብራርተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋሙ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ኃይል ልማት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ትምህርትና ሥልጠና በተማረ የሰው ሀብት አቅርቦት ላይ ብቻ ሳይወሰን የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ፣ ምርምርና ፈጠራን ማበረታታት እንዲሁም ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልገውን ብቁ ባለሙያ ማቅረብ ላይ ያተኮረ መሆኑንም አመልክተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር፣ ም/ዋና ዳይሬክተሮች በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተዋል።