Habtamu Mulugeta (PhD)

የጥናትና ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሐብታሙ ሙሉጌታ

የኢንስቲትዩቱ ስምንተኛ ሳምንት የጥናትና ምርምር ሴሚናር የእሴት ሰንሰለት ትንተና ለስልጠና ጥራት እና አግባብነት ያለው ፋይዳ ላይ ትኩረታቸውን ባደረጉ ሁለት የጥናት ውጤቶች ላይ ተመስርቶ ተካሄደ።
**************ህዳር 25/2017********
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ስምንተኛ ሳምንት ጥናትና ምርምር ሴሚናር የባዮሜዲካል ቁሳቁሶችን ጥገና ዋና ጉዳዩ ባደረገ እና በቴክስታይል ኢንደስትሪ የባለድርሻ አካላትን ሚና መለየት ላይ የእሴት ሰንሰለት ትንተና በተሰራባቸው ሁለት የጥናትና ምርምር ውጤቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሐብታሙ ሙሉጌታ የእሴት ሰንሰለት ትንተና መሠረት ያደረጉ ጥናትና ምርምሮች ቀጣይነት ባለው መልኩ ለውይይት እንደሚቀርቡ ገልጸው በዛሬው ዕለት የቀረቡ ሁለት ጥናት ጽሁፎች ወሳኝ ርዕሰጉዳዮች የያዙ መሆናቸውን አንስተዋል።
የህክምና ተቋሞቻችን ጥራት ያለው አገልግሎት እንዳይሰጡ እንቅፋት ከሚሆኑባቸው መካከል የህክምና ቁሳቁሶች ብልሽት ተጠቃሽ እንደሆነ ያነሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን ሊፈታ በሚችል መልኩ በጥናት የተለየ ስልጠና መስጠት አስፈላጊነው ብለዋል።
ይህ ችግር ስልጠና ፕሮግራሞች ሊከፈቱለት የሚገባ ዘርፍ መሆኑን በአገር አቀፍ የፕሮግራም ክለሳ ጥናት ከለያቸው መካከል አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ኢንደስትሪዎች አብረው መስራት እንዳለባቸው ቢታወቅም የስልጠና ተቋማት ድርሻ እና የኢንደስትሪዎች ድርሻ በትክክል ተለይቶ ባለመቀመጡ በሚፈለገው ደረጃ ለመስራት እንቅፋት እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ሐብታሙ በሁለተኛነት የቀረበው የጥናት ጽሁፍ መሠል ችግሮችን ለመፍታት መፍትሄ አመላካች እንደሆነ ገልጸዋል።
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የእሴት ሰንሰለት ትንተና ጉዳይ ኢንስቲትዩቱ በደረጃ ስምንት በሚጀመርባቸው ፕሮግራሞችም ተጠንቶ መቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል።