የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር የ4.5 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር አካል የሆነውና ተጠሪ ተቋማትን ያሳተፈው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ምስራቅ ሸዋ ዞን በአዱላላ ተራራ ተካሔደ፡፡

Federal TVET Institute

July 6, 2020

የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት፣ የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲን ጨምሮ አራቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ተጠሪ ተቋማት እና በዙሪያ አካባቢዎች ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ያሳተፈ የሁለተኛው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግርብር ሰኔ 22/2012 ዓ/ም በአዱላላ ቀበሌ ተካሂዷል፡፡ 

ዓለማችን ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው የሰው ልጅ በሚፈጥረው ተጽእኖ ምክንያት እየተረበሸች እና እየተቸገረችም ትገኛለች፡፡ ዋነኛው ተጽዕኖው ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ፣ በአህጉራችን አፍሪካ በ2063 የልማት ግቦች ውስጥ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ 

ይህንኑ ቀድማ የተረዳችው ሀገራችን መላ ህዝብን ባሳተፈ ሁኔታ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በስፋት እየተገበረች ትገኛለች፡፡ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) በታወጀውና ሁለተኛ ዓመቱን በያዘው የ2012ዓ/ም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል፡፡ 

በአገራችን በቴክኒክና ሙያ ትምርትና ስልጠና እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን ሰፊ የሰው ሀይል በማንቀሳቀስ ይህንን መርሀ-ግብር ለመፈጸም ያቀደው የኢፌዲሪ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴርም 4.5 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል የያዘውን እቅድ ሰኔ 8/2012 በይፋ አስጀምሯል፡፡

የዚሁ መርሀ-ግብር አካል የሆነው እና በሚንስትር መስሪያ ቤቱና በአራቱ ተጠሪ ተቋማት የሚፈፀመው 35ሺህ ችግኞችን ለመትከል እቅድ የተያዘለት ፕሮግራም በምሥራቅ ሸዋ ዞን በሚገኘው በአዱላላ ተራራ በሀያ አምስት ሄክታር ላይ ተካሂዷል፡፡ ይህ ተከላ ሥነ-ሥርዓት በአመራር ደረጃ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይ የሁሉም ተቋማት ሰራተኞች ተከላ እንደሚያካሒዱ ተነግሯል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንሰቴሯ ፕ/ር ሒሩት ወ/ማርያም ሥነ-ሥርዓቱን በንግግር ሲከፍቱ ‹‹አረንጓዴ አሻራ የልማትና የብልጽግና ብቻ ሳይሆን የህልውናና የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ነው›› ብለዋል፡፡ የቱሪዝም ምንጭ፣ የኢንዱስትሪ ግብአቶች የምናገኝበት ፀጋችን መሆኑን ያስታወሱት ሚንስትሯ የባህል መድሀኒቶት የሚሆኑ እጽዋትን የምናገኝበት መንገድ ነው ብለዋል፡፡

በተራራው ላይ የሚተከሉ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ እጽዋትን እንደምሳሌ በመጥቀስም ‹‹አረንጓዴ አሻራ ምግብና መጠጥ ነው፤ የምግብ ዋስትናችን የምረጋግጥበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ልንረባረብበት የሚገባው›› ብለዋል፡፡

በእለቱ የፓናል ውይይት የተካሔደ ሲሆን በቀጣይ ቦታውን የምርምር ማዕከል ለማድረግ ስለሚሰሩ ስራዎች፣ ስለሚተከሉ እጽዋትና ሥነምዳራዊ ሁኔታው ከምሁራን ሀሳብ ተነስቷል፡፡ ለዚህም ከአካባቢው መስተዳድር ጋር ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚቆይ ስምምነት የተካሔደ ሲሆን 25 ሄክታር ቦታ ካርታ ተሰርቶለት ርክክብ ተካሂዷል፡፡ 

በቀጣይም እያንዳንዱ የትምህርት ተቋም ቦታ በስሙ ተረክቦ የሚያለማበት እና የሚንከባከብበት አቅጣጫ ተቀምጧል ተብሏል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti