በኢንስቲትዩቱ የተሰሩ ለአገራችን የመጀመሪያ የሆኑ ተኪ ቴክኖሎጂዎች ይፋ ተደረጉ።

በኢንስቲትዩቱ የተሰሩ ለአገራችን የመጀመሪያ የሆኑ ተኪ ቴክኖሎጂዎች ይፋ ተደረጉ።
**********ጥቅምት 19/2018*********
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በራስ አቅም የተመረቱ ተኪ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ያስተዋወቀበት መርሀግብር አካሂዷል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንደአገር በቴክኖሎጂ ፈጠራ ያመጣነው ውጤት የሉአላዊነት መገለጫ፣ የተሟላ አገራዊ ነጻነት ማረጋገጫ መንገዶች ናቸው ብለዋል።
ክብርት ሚኒስትሯ ኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን የአገር ችግር የሚፈቱ ፈጠራዎችን እያሳካ መሆኑን አንስተው በመደመር መንፈስ መሥራት መቻሉ አቅም እንደሆነው አንስተዋል። የግሉ ዘርፍ፣ የመንግስት ተቋማትም አብረው መስራታቸው አግዟል ብለዋል።
የክህሎት ኢትዮጵያ ፕሮግራም በአገራችን ፈጠራን ያበረታታ የተደበቁ አቅሞችን ወደፊት ያመጣ የቴክኖሎጂ ፕሮግራም እንደሆነ ክብርት ሚኒስትሯ ጨምረው ገልጸዋል።
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር እንደአገር ፈጠራን ማበረታታት የሚገባን ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ ቴክኖሎጂ የመፍጠር፣ በስፋት የማምረት ተልዕኮ በስኬት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ብሩክ ኢንስቲትዩታችን በአገራችን የትኩረት መስክ በሆኑ ዘርፎች ላይ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ስንሰራ ቆይተናል፤ ትልቅ ውጤትም አግኝተናል ብለዋል።
በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠሩ እና በዛሬው ዕለት ያስተዋወቅናቸው ፈጠራዎች ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ያለውን አመለካከት እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።
የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጸዳለ ተክሉ በበኩላቸው እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የደረሱበት ውጤት መፍጠር እና አካባቢያቸውን ማዳመጥ የቻሉ ወጣቶች እንዳሉን ያየንበት ነው ብለዋል።
ለዚህ ውጤት መብቃት የተለያዩ ተቋማት ትብብር ውጤት መሆኑን ገልጸው ኢንስቲትዩቱ፣ ኢንተርፕራይዙ፣ የግሉ ዘርፍ፣ ስታርታፖች ተቀናጅተው ያመጡት ውጤት ነው ብለዋል።
በዛሬው ዕለት ሦስት ቴክኖሎጂዎች እና ስድስት ሶፍትዌሮች ተመርቀዋል። የማሽን አንቀሳቃሽ ሞተር (Induction Motor)፣ የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጀር እና ስማርት የመብራት ፖል ሦስቱ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች ናቸው።