በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ሮቦቲክስ ፕሮግራሞች በአገራችን የመጀሪያ የሆነ የደረጃ 6 (መጀመሪያ ዲግሪ) ስልጠና ለማስጀመር የሚያስችል ስምምነት ተካሄደ። *******መስከረም 14/2018********
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር ከኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱም በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ሮቦቲክስ ፕሮግራሞች በደረጃ 6 (መጀመሪያ ዲግሪ) ስልጠና ለማስጀመር የሚያስችል ነው።
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር እንደአገር በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና ሮቦቲክስ መስኮች የሰለጠነ የሰው ሀይል ፍላጎት መኖሩን ገልጸው የሁለቱ የተቋማት ትብብር የህዝባችንን አዳጊ ፍላጎት የመመለስ አካል አድርገን እንወስደዋለን ብለዋል።
ስርዓተስልጠና (curriculum) ተዘጋጅቶ መጠናቀቁንና ስልጠናውም በዚህ ዓመት እንደሚጀመር ገልጸው በዝግጅቱ ላይ አርቴፊሻል ኢንስቲትዩቱ ሲሳተፍ መቆየቱን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው ለአገራችን የሰለጠነ የሰው ሐይል ፍላጎት ኢንስቲትዩቱ በረጅምና አጫጭር ስልጠናዎች እየሰራ ያለውን ስራ አድንቀዋል።
ይህ ፕሮግራም በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን ፕሮግራም በኢንስቲትዩቱ እንዲሰጥ ማስቻሉ በዘርፉ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።





