አካል ጉዳተኞች በክህሎት ስልጠና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የስልጠና ተቋማትን ምቹ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚሰራ ተገለጸ። **መጋቢት 19/2017 ዓ.ም**

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የአካል-ጉዳተኞች አካቶ ቴክኖሎጂ ማዕከል ስራውን ዛሬ ለባለድርሻ አካላት ይፋ አደርጓል።
በእለቱ የተካሄደውን የፓናል ውይይት እና የትውውቅ መርሃግብር ያስጀመሩት የጥናትና ምርምር፣ ማህበረብ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሙሉጌታ (ዶ/ር)፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ለአካል-ጉዳተኞች ምቹ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ይህንን ልምድ በመቅረፍ አካል-ጉዳተኞችን ያካተተ የስልጠና፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ክህሎት አማራጮችን በማስፋት ለዕኩል ተጠቃሚነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ አካታች የሆነ ምቹ ከባቢን ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ም/ዋና ዳይሬክተሩ በክህሎት ኢትዮጵያ ፕሮግራም የሚፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችም አካል ጉዳት ያለባቸው ወገኖችን ለማገዝ የሚችሉ ፈጠራዎች እንዳሉበት ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ ላይ አካል ጉዳተኞች የሠሯቸው ፈጠራዎች እና አካል ጉዳት ላለባቸው ወገኖች አጋዥ የሆኑ የፈጠራ ውጤቶች ቀርበዋል።
አካል-ጉዳተኞች በክህሎት ስልጠና ተጠቃሚ መሆን በዓለምአቀፍና አገር አቀፍ ህጎች መካተቱን በማስታወስ፣ ይህ መብት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በተገቢው ሁኔታ መተገበር እንዳለበት የጠየቁት የኢንስቲትዩቱ የአካቶ ቴክኖሎጂ ማዕከል አስተባባሪ አሰልጣኝ ጥሩየ አበበ ናቸው።
ከኢንስቲትዩቱ ጋር እየሠራ የሚገኘው የኢትዮ ኢምፓወር ኤብሊቲስ መስራች ወ/ሮ ዓለምጸሃይ ካህሳይ ማዕከሉን ተጠቅመው ድጋፍ ለሚገባቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተነሳሽነታቸውን ገልጸዋል።
አካል-ጉዳተኞች በትምህርትና ስልጠና ዕኩል ተጠቃሚ ያለመሆናቸውን በፓናል ውይይት ላይ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ባለድርሻ አካላት ያመለከቱ ሲሆን ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ስራው መጠናከር አለበት ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን፣ የአዲስ አበባ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ እና ሌሎች መንግስታዊ መንግስታዊ ያልሆኑ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በመርሃግብሩ ላይ ተሳትፈዋል።