KFW የኢንስቲትዩቱን የቴክኖሎጂ ልማት ስራዎች ለመደገፍ እንደሚሰራ ተገለጸ። *****************መጋቢት 16/2017*************

የጀርመን መንግስት የኢንቨስትመንትና የልማት ባንክ (KFW) የፖርትፎሊዮ ማናጀር በሆኑት ሚስ ዳቪና ሺፔርስ የተመራ የልዑካን ቡድን ኢንስቲትዩቱ የጀመራቸውን የቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ስራዎች እንዲሁም በጀርመን መንግስት ድጋፍ የተጠናከሩ የስልጠና ክፍሎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የጉብኝቱ ዓላማም ባንኩ የጀመረውን ትብብር ለማጠናከር እና በአዳዲስ ፕሮጀክቶች የኢንስቲትዩቱን የክህሎት ልማት ስራዎች ለመደገፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠርን ያለመ እንደሆነ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ለልዑካን ቡድኑ ባደረጉት ገለጻ ኢንስቲትዩቱ ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ “ክህሎት ኢትዮጵያ” በሚል ችግር ፈቺ የሆኑ ተኪ ቴክኖሎጂዎች የሚመረትበት ሁኔታ መጀመሩን በዚህም በርካታ ቴክኖሎጂዎች መፈጠራቸውን አብራርተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ ጥራት ያለው ስልጠናን ለመስጠት እየተጋ መሆኑን በዚህም ስልጠናን ከምርት ጋር ማስተሳሰር የሚያስችል አዲስ ስልት ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ ጅምር ስራዎች ይበልጥ ውጤት እንዲያመጡ በተለይም የፈጠራ ስራዎች በብዛት ተመርተው ወደ ተጠቃሚው እንዲደርሱ የረጂ ድርጅቶች ሚና ቁልፍ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ብሩክ KFW ከዚህ አንጻር ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የክህሎት ኢትዮጵያ ተሳታፊዎችም በኢንስቲትዩቱ እያበለጸጓቸው ያሉ የፈጠራ ስራዎችን አቅርበዋል።
የKFW ሥራ ሀላፊዎች ኢንስቲትዩቱ የጀመራቸውን የቴክኖሎጂና ፈጠራ ስራዎች፣ በሪፎርም ስራዎች ባስመዘገባቸው ለውጦች መደነቃቸውን ገልጸው ተቋማቸው በአዳዲስ ፕሮጀክቶች ኢንስቲትዩቱን የክህሎት ልማት ስራዎች ለመደገፍ እንደሚሰራም ቃል ገብተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ልማት ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀዳለ ተክሉ እና የስልጠናና አቅም ግንባታ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ሐፍቶም ገ/እግዚአብሔር (ረ/ፕሮፌሰር)፣ የKFW በኢትዮጵያ ሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።