ቦርዱ የቴክኖቢዚያ የኢንደስትሪ ውጤቶች ኢንተርፕራይዝ የ6 ወራት አፈጻጸምን ገመገመ፡፡ ****ጥር 30/2017*****

ቦርዱ የቴክኖቢዚያ የኢንደስትሪ ውጤቶች ኢንተርፕራይዝ የ6 ወራት አፈጻጸምን ገመገመ፡፡
****ጥር 30/2017*****
በኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ቴክኖቢዚያ የኢንደስትሪ ውጤቶች ኢንተርፕራይዝ የበጀት ዓመቱን የ6 ወራት ዕቅድ ፈጻጸም ለቦርዱ አቅርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
ኢንተርፕራይዙ የያዛቸው ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ የመደበኛ ስራዎች ዕቅድ አፈጻጸም የውይይት አጀንዳ ሲሆኑ የኦዲት ሪፖርትም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ እና የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር ከተመሰረተ አንድ ዓመት የሞላው ኢንተርፕራይዙ ከምስረታ እና የዝግጅት ጊዜ አልፎ በርካታ ተግባራትን መፈጸም መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ኢንተርፕራዙ ለመሰል ተቋማት ሞዴል ተቋም እንዲሆን ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጸዳለ ተክሉ በበኩላቸው ኢንተርፕራይዙ ሲቋቋም የተለመዱ ስራዎችን ለመስራት ሳይሆን በዘርፉ አዲስ ባህል ለመፍጠር ነው ብለዋል።
በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ከውጪ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን ማምረት መቻሉ ትልቅ እመርታ ነው ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሯ በተለያዩ መለኪያ መስፈርቶች ተወዳዳሪነቱን ማጠናከር አለበት ብለዋል።
የኢንተርፕራይዙ ስራአስኪያጅ አቶ ለሚ ቱጆ ባለፉት ስድስት ወራት የተፈጸሙ ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል። በሪፖርታቸውም በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎችን አቅርበል፡፡
እንደአገር የመጀመሪያ የሆነ የተሸከርካሪ ጎማ መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል ፋብሪካ በራስ አቅም ተሰርቶ ወደስራ መግባቱን በትልቁ የጠቀሱት አፈጻጸም ነው፡፡
ቴክሎጂዎችን በስፋት የማምረት ስራ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይም ሌሎች ላይ ለመስራት የቴክኖሎጂ ልየታ መካሄዱን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ረጃጅም ወንዞችን የሚሻገሩ ተንጠልጣይ ድልድዮችን ሰርተው ለተጠቃሚው ማድረስ መቻሉንም ስራአስኪጁ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።
በሥራናክህሎት ሚኒስቴር በኩል ለዓለምአቀፍ የስራ ገበያ ብቁ የሆኑ ሾፌሮችን የማሰልጠን ስራ እየተሰራ መሆኑም ሌላው ኢንተርፕራይዙ በስኬት ከፈጸማቸው ተግባራት መካከል ተጠቅሷል፡፡
“እያመረትን እናሰለጥናለን” በሚል መርህ የተቋቋመው ኢንተርፕራይዙ ይህንኑ ተልዕኮ ለማሳካት ከኢንስቲትዩቱ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑ ገልጸው ይበልጥ ትስስሩን ለማጠናከር የአሰራር ማንዋል የተዘጋጀ ሲሆን በቀጣይ ለቦርድ ይቀርባል ብለዋል።
በጋርመንት እና ሌዘር ዘርፎ የተማሪዎች ዩኒፎርም ማምረት፣ ቦርሳ ማምረት እንዲሁ ከበርካታ የፕሮጀክት አፈጻጸሞቹ መካከል የተነሳ ነው፡፡
የቦርድ አባላትም ኢንተርፕራይዙ በአጭር ጊዜ ትልቅ ትምህርት ሊወሰድበት የሚችል አፈጻጸም መፈጸም መቻሉን አድንቀው ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል ያሏቸውን ሐሳቦች አንስተዋል።
በመጨረሻም የቦርዱ ሰብሳቢ ዶ/ር ብሩክ ከድር እስከ ቀጣዩ የቦርድ የግንኙነት ጊዜ ሊሰሩ ይገባል ያሏቸውን አቅጣጫዎች አስቀምጠው ውይይቱ ተጠናቅቋል።