የኢንስቲትዩቱ የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ። *******ጥር 9/2017****

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ የተቋሙ ስራሀላፊዎች፣ ሥራአስፈጻሚዎች፣ ቡድን መሪዎች ፈካሊቲ ዲኖች እና ትምህርት ክፍል ሐላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር መድረኩን በከፈቱበት ጊዜ እንደገለጹት ዓመቱን ስንጀምር የማጽናት ዓመት በሚል በሁሉም ሙያተኞች ዘንድ በራዕይ መጋራት የተጀመረ ዓመት መሆኑን አስታውሰው ዓመቱን የልህቀት ትልም ለማሳካት በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ ግቦቹን ለማሳካት የተለያዩ ሪፎርም ቡድኖች ተዋቅረው እየተሰሩ እንደሆነ በዚህም መደበኛ ስራን በሪፎርም እሳቤ እየተመራ በመሄዱ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ያለፉት ስድስት ወራት በተቀናጀ አመራር ሰጪነት፣ ተቋማዊ አቅምን በማስተሳሰር መሥራት በመቻሉ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል ።
የአስተዳደር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ አዋቶ ለውይይት መነሻ የሆነ ሪፖርት ሰነድ አቅርበዋል። በሪፖርታቸውም በርካታ ስኬቶችን ዘርዝረዋል። ኢንስቲትዩቱ ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በዋናው ግቢ አይሶ 9001:2015 እውቅና ማግኘቱን አስታውሰው በተያዘው ዓመት በቴክኖሎጂ ማምረትና ብየዳ ልህቀት ማዕከል ISO 17025 እና በሐዋሳ ካምፓስ ISO 9001 እውቅና ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የዓለም አቀፍ ክህሎት ውድድር ኢትዮጵያን አባል ማድረግና በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ መደረጉ ተጠቃሽ ስኬት ነው።
ኢንስቲትዩቱ ጥራት ያለው ስልጠናንና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን የሚመሩበት የአጫጭር ስልጠና፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የብዝሐምርት ፍኖተ-ካርታዎች መዘጋጀታቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። በተጨማሪም የስልጠና ጥራትን የሚያስጠብቁ የስልጠና ጥራት ኮሚቴ እና የዳይሬክተሮች ፎረም ተዋቅረው ወደስራ መግባታቸው ተገልጿል።
በደረጃ ስምንት ሁለት ፕሮግራሞች ለመክፈት በተሰራ ስራ ወደ መጨረሻ ምዕራፍ መድረሱ ትልቅ ውጤት ከሚባሉት መካከል አንዱ ሆኖ በሪፖርቱ ተነስቷል። በመደበኛ ፕሮግራም እና በአጫጭር ፕሮግራምች በርካታ ዜጎችን እያሰለጠነ መሆኑም ተጠቅሷል።
ባለፉት ስድስት ወራት ሳምንታዊ ጥናትና ምርምር ሴሚናሮች ሳይቆራረጥ መካሄዱ፤ የገበያውን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ፕሮግራሞችን ለመክፈት የሚያስችሉ ስድስት ዘርፎች ላይ የእሴት ሰንሰለት ትንተና ጥናቶችን ጨምሮ በርካታ የምርምር ስራዎች መካሄዳቸው የተጠቀሰ ሲሆን ። ሁለተኛ ቅጽ የቴክኒክና ሙያ ጆርናል ለህትመት ከመብቃቱም በላይ የኦንላይን ፕላትፎርም የተዘጋጀለት መሆኑ ተያይዞ ተነስቷል።
ቴክኒክና ሙያስልጠና ተቋማትን የተለያዩ የስልጠና እና የቢሮ ቁሳቁሶችን በመደገፍ የማጠናከር ስራ የተሰራ ሲሆን ከዚህም መካከል ለሱሉልታ፣ ለመሐል ሜዳ፣ ለሚዛንአማን ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች ከ15ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ቁሳቁሶች ደግፏል። በተጨማሪም ለአቅመደካማ ዜጎች ቤት ሰርቶ እያስረከበ ይገኛል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የተበላሸ የመኪና ጎማን መልሶ ለተለያዩ ምርቶች መጠቀም የሚያስችል ፋብሪካ አምርቶ ማቋቋም መቻሉ አንዱ ኢንስቲትዩቱ የሰራው ትልቅ ስኬት ሆኖ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ በመጀመሪያው ዙር ክህሎት ኢትዮጵያ የተመረቱ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ለማምረት በተያዘው ስራ 23 ቴክኖሎጂዎች ተለይተው፣ 11 ያህሉም ስፔስፊኬሽን የወጣላቸው ሲሆን ሰባቱ ወደ ብዝሐ ምርት መግባታቸው ተገልጿል።
የኢንስቲትዩቱ ኢንተርፕራይዝ ተጠናክሮ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ፕሮጀክቶችን እየሰራ መሆኑ ሌላው በስኬትነት ቀርቧል።
አለምአቀፍ ትብብሮችን በማጠናከር የኢንስቲትዩቱን አቅም ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑ በዚህም ውጤት እየተመዘገበ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ብሩክ በኢንስቲትዩቱ እየተተገበሩ ያሉ ዋናዋና ፕሮጀክቶችን መረጃ ሰጥተዋል።
በግብርና መስክ እየተሰሩ ያሉ፣ የስራቦታን ምቹ የማድረግ፣ የልህቀት ማዕከላት ግንባታ እና ሌሎችንም ስራዎች አቅርበዋል። በእነዚህ ፕሮጀክቶች ውጤት የውስጥ አቅምን በማስተሳሰር ተግባራት እየተሰራ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። ፕሮጀክቶች ስልጠናዎችን ተግባርተኮር ለማድረግ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተሳታፊዎችም ኢንስቲትዩቱን ራዕይ ከልብ ተጋርተነዋል ብለዋል። ለዚህም ነው ውጤቶችን እያስመዘገብን ያለነው ብለው በቀሪ ወራትም ጅምሮችን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና ኢንስቲትዩቱን መሪ ተቋም የማድረግ ጅምር ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።