የኢንስቲትዩቱ የስልጠና እና አቅም ግንባታ ዘርፍ የ2017 የበጀት ዓመቱ የ6ወራት እቅድ አፈጻጸም ተገመገመ። የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የስልጠናና አቅም ግንባታ ም/ዋና ዳይሬክተር ሐፍቶም ገ/እግዚአብሔር (ረ/ፕሮፌሰር) የበጀት ዓመቱን የስልጠና ስራዎች ገምግመዋል።

በግምገማውም ዓመተ-ልህቀት ፪ ተብሎ በተሰየመው 2017 የሥልጠና ጥራትን ለማስጠበቅ እና በዚህም ልህቀት ለማምጣት የተሰሩ ስራዎች ተዳስሰዋል። ስልጠናዎች ይበልጥ ተግባር ተኮር እንዲሆን በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የተሰራው ስራ መልካም አፈጻጸም እንዳለው በሪፖርቱ ተዳስሷል።
ሌላው ጥምር የስልጠና ስልት (blended learning) ተግባራዊ ለማድረግ በተለይም ባለፉት ዓመታት የነበሩ ጅምሮችን በማስፋት እየተሰራ መሆኑን ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የኢንስቲትዩቱ የስልጠና ዘርፍ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ያሉበትን ተቋማዊና አገራዊ ተልዕኮዎች በብቃት ሊወጣ ይገባል ያሉት ረ/ፕሮፌሰር ሐፍቶም ከእነዚህ መካከልም የመውጫ ፈተናን ቀደም ብሎ በመዘጋጀት በጥራት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አያይዘውም በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በኢንስቲትዩታችን የሚዘጋጀው አራተኛው አገርአቀፍ የክህሎት ውድድር እንደተቋም ያለንን ድርሻ በብቃት መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሰልጣኞች መመረቂያ ፕሮጀክቶቻቸውን በብቃት ሰርተው እንዲመረቁ አስፈላጊ ግብአቶች እንዲሟሉ ይደረጋል ያሉ ሲሆን በአጠቃላይ በአካዳሚክ ካሌንደሩ የተቀመጡ ተግባራት በጊዜያቸው እንዲከናወኑ እንደሚሰራ ገልጸዋል።