ኢንስቲትዩቱ የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል የሚሆን ‹‹የ21ኛው ክፍለዘመን ማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት ቤት›› መገንባት ጀመረ። ************ጥር 02/2017 ዓ.ም***************

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ኢንስቲትዩቱ የሚያስገነባውን የ21ኛው ክፍለ-ዘመን ማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት ቤት ግንባታ በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻ፣ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች እና የኢንስቲትዩቱ አሰልጣኞች ተገኝተዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ግንባታውን ሲስጀምሩ ‹‹ይህ ትምህርት ቤት እያንዳንዱ ተማሪ ምን ክህሎት አለው የሚለውን ለይቶ በማውጣት በክህሎቱ እና በፍላጎቱ ልክ ስልጠና ማግኘት የሚችልበት ማዕከል ይሆናል ብለዋል፡፡
በአዲሱ የአገራችን የትምህርትና ስልጠና ፓሊሲ ላይ የተቀመጠውን ቮኬሽናላይዜሽንን ለማሳካት ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ መሠል ተቋማትን መገንባት ይገኝበታል ብለዋል፡፡
ይህ ፕሮጀክት መጀመሩ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓትን በአወንታዊ መንገድ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር በበኩላቸው የ21ኛው ክፍለ-ዘመን ማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት ቤት የክህሎት ማሳደጊያ ቦታ እንዲሆን ታስቦ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ዜጎች ለሙያና ክህሎት ያላቸውን አመለካከት እንዲያድግ እና ክህሎት ያለው ዜጋ እንዲጨምር ከልጅነት ጀምሮ ማስተማር፣ ማሰልጠን ይገባል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህ ትምህርት ቤት ከህጻንነታቸው ጀምሮ ፍላጎታቸውንና ችሎታቸውን መሰረት አድርጎ ስልጠና በመስጠት ይህንን ያሳካል ብለዋል፡፡
ግንባታውም በተለያዩ ደረጃዎች የሚፈጸም ሲሆን የመዋዕለ-ህጻናት ትምህርት ቤት በመጀመሪያ ዙር የሚገነባ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ግንባታ እስከ ከፍተኛ ስልጠና ተቋማት መግቢያ ድረስ እንደሚይዝ ተናግረዋል፡፡
የመጀመሪያ ዙር ግንባታ የህጻናት መጫወቻን ጨምሮ በ1 ሺ 6 መቶ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚሰራ ሲሆን ከሁለት ወራት በኋላ ተጠናቆ ለስራ ዝግጁ እንደሚሆን ግንባታውን የጀመረው የግንባታ ተቋራጭ ገልጿል።