በኢንስቲትዩቱ ዓለምአቀፍ ብየዳ ስልጠና የወሰዱ የሁለተኛ ዙር ሰልጣኞች ተመረቁ። *******ታህሳስ 20/2017 ዓ.ም*******

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የበጀት ዓመቱን ሁለተኛ ዙር የብየዳ ሰልጣኞች አሰልጥኖ አስመርቋል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር ስልጠናቸውን አጠናቅቀው እና ተመዝነው ብቁ ለሆኑ ሰልጣኞች ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያለውን የምስክር ወረቀት የሰጡ ሲሆን በዚሁም ባስተላለፉት መልዕክት ኢንስቲትዩቱ ዓለምአቀፍ ደረጃ ያሟሉ ብቁ በያጆችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የኢንስቲዩቱ የቴክኖሎጂ ማምረትና የብየዳ ልህቀት ማዕከል ዓለምአቀፍ እውቅና ያለው መሆኑን እንዱሁም አለምአቀፍ እውቅና ያላቸው አሠልጣኞች ስልጠና እየሰጡበት መሆኑን ገልጸው ቁጥራቸውን ለማስፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ የጥራት ደረጃውን ለማሳደግ እየሰራ ባለው ስራ የወርክሾፕ ጥራትን የሚያረጋግጠውን እና የምዘና ስራውን የሚያዘምነውን አይሶ 17025 እና 17024 እየተገበረ ይገኛል ብለዋል። ይህም ዓለምአቀፍ ብቃት ያላቸውን ሙያተኞች ለማፍራት ምዘናውም ይብልጥ ጥራት ያለው እንዲሆን ያስችላል የገበያውን ፍላጎት የሚያሟሉ ሙያተኞችን ለማፍራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ሰልጣኞች ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ አሰልጣኞችን ጨምሮ ከሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕና ሌሎች ተቋማት የመጡ አርባ ሰልጣኞች ተሳታፊዎች ሲሆኑ ስልጠናውም በማግ(MAG)፣ አርክና(ARC) ቲግ(TIG) የብየዳ ዘርፎች እንደተሰጠ ተገልጿል።
ሰልጣኞችም ባገኙት ክህሎት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ዊንታ አትክልቲ ከውቅሮ ግብርና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ለዚህ ስልጠና የመጣች ሲሆን በስልጠናው የተገኘው የተግባር ልምድ ለማኑፋክቸሪንግ ሙያ በጣም አስፈላጊ ነው ብላለች።
ከሜድሮክ ኩባንያ የመጣው ካሳሁን ላቀው እንደሚለው ከሆነ ከዚህ ቀደም እሱ ከሚጠቀመው የብየዳ ሙያ በኢንስቲትዩቱ መጥቶ ያገኘው ዘመናዊና ቀለል ባለ መንገድ ብየዳን ለመፈጸም የሚያስችል አቅም ጨምሯል።
አሰልጣኝ እታገኝ ውብሸት እና ፋኖስ ድልነሳው በጥራት ብየዳን የሚሰሩ ባለሙያዎችን እጥረት ለመቀነስ በሙያቸው እየሰሩ ሲሆን ሴቶች በሙያው ጥሩ ልምድ እያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል።
በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ማምረትና ብየዳ ስልጠና ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰላሙ ይስሃቅ (ዶ/ር) በበኩላቸው በጥራትና በከፍተኛ ደረጃ ማሰልጠን የሚችሉ እንስቶችን ከመላው አገሪቱ ለይተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።