የኢንስቲትዩቱ ስድስተኛ ሳምንት ጥናትና ምርምር ሴሚናር በዘርፉ ገጽታ ግንባታ ስራ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተካሄደ፡፡ ***********ህዳር 11/2017************

የኢንስቲትዩቱ ስድስተኛ ሳምንት ጥናትና ምርምር ሴሚናር በዘርፉ ገጽታ ግንባታ ስራ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተካሄደ፡፡
***********ህዳር 11/2017************
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በበጀት ዓመቱ ስድስተኛ ሳምንት የጥናትና ምርምር ሴሚናር በቴክኒክና ሙያ የገጽታ ግንባታ ላይ እና በዘርፉ አመራር ሚና ላይ ትኩረታቸውን ባደረጉ ሁለት ጥናት ጽሁፎች ላይ አተኩሮ አሰልጣኞች እና ሰልጣኞች ተሳትፈውበት ተካሄደ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምርና ማህረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀብታሙ ሙሉጌታ የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ሴሚናር እያደገ የመጣ፣ ግቡን እየመታ የሚገኝ ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡
በዕለቱ ከቀረቡት የጥናት ጽሁፎች መካከል አንዱ ከሁለተኛው የጥናትና ምርምር ጆርናል ላይ መሆኑን ገልጸው ለቴክኒክና ሙያ ስርዓት እድገት አጋዥ ናቸው ብለዋል፡፡
ቴ/ሙያ ለአንድ አገር ለውጥ ጉልህ ሚና ያለው፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በየዓመቱ እያፈራ የሚገኝ ስርዓት ቢሆንም አሁንም ግን በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ቦታ የሚገባውን ያህል አይደለም ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩታችን የዘርፉን ገጽታ ግንባታ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ ጉዳይ ተደጋጋሚ ውይይት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የአመራር ሚና ለዘርፉ እድገት ያለውን ላቅ ያለ ሚና ያነሱት ዶ/ር ሀብታሙ በዚህ ጉዳይ ላይ ተመስርቶ ለውይይት መነሻ ሰነድ መቅረቡንም አድንቀዋል፡፡
የመጀመሪው ጽሑፍ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ገጽታ ግንባታ ጉዳይ ላይ ያተኮረውና Enhancing Image Building and Employability through Higher TVET in Developing Countries: Opportunities, Challenges, and Future Prospects የሚል ርዕስ የተሰጠውን ጽሑፍ አዘጋጅተው ያቀረቡት ዶ/ር ተሾመ ለማ ለ37 ዓመታት በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ከባለሙያነት እስከ ሚኒስትር ዴኤታነት ያገለገሉ፣ በአሁኑ ጊዜም በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ እና የአገራችን የቲንክታንክ ቡድን ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ያሉ ናቸው።
ዶ/ር ተሾመ ለማ በጽሑፋቸው በዘርፉ ያሉ አገርአቀፍ እና ዓለምአቀፍ ተሞክሮዎችን፣ ተግዳሮቶችንና መፍትሔዎችን ዳስሰዋል፡፡
የፖሊሲ ጉዳዮች፣ የመሰረተ-ልማት ችግሮች፣ ከኢንዱስትሪ ጋር ያለ ትስስር ማነስ፣ የአሰልጣኞች አቅም ጉዳይ ዘርፉ ማደግ ባለበት ልክ እንዳያድግ አድርገውታል፤ ያለውን ተቀባይነት አሳንሰውታል ብለዋል፡፡
ዘርፉ ተቀባይነቱ እንዲያድግም ሊሰሩ ይገባል ያሏቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ስርዓተ-ስልጠናውን ማዘመን፣ የግሉን ዘርፍ ትብብር ማሳደግ፣ ኢንተርፕረነርሺፕን ማጠናከር፣ ዓለምአቀፍ ልምዶችን ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮችና ቴክኖሎጂዎችን በመላ አገሪቱ በሥርዓቱ ውስጥ የሚሰፉበት ሁኔታ ቢፈጠር ዘርፉን ተቀባይነቱን እንደሚጨምረውም ገልፀዋል፡፡
ሁለተኛውና Roles of Leadership in Successful Organizational Change Management: A Theoretical Review የሚል ርዕስ የተሰጠው ጽሑፍ የኢንስቲትዩቱ አሰልጣኝ በሆኑት ዶ/ር በክረጺዮን ሐይለስላሴ የቀረበ ሲሆን ለተቋማት ለውጥ የአመራር ሚና የማይተካ በመሆኑ በአመራር አቅም ግንባታ ስራ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡