የአፍሪካ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲዎችና ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጆች ማህበር (ATUPA) ዋና ፀሀፊ በኢንስቲትዩቱ ጉብኝት አካሄዱ። ************ህዳር 6/2017***********

የክህሎት ልማትን ማጎልበት እና በአህጉሪቱ ወጥነት ያለው ሥርዓተ ስልጠና እንዲኖር የፖሊሲ ሐሳቦችን በማመንጨት እየሰራ የሚገኘው “የአፍሪካ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲዎችና ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጆች ማህበር (ATUPA)” የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት አባሉ እንዲሆን በዋና ጸሐፊው በኩል ጥሪ አስተላልፏል።
የኢንስቲትዩቱ የስልጠናና አቅም ግንባታ ም/ዋና ዳይሬክተር ሐፍቶም ገ/እግዚአብሄር (ረ/ፕሮፌሰር) የአፍሪካ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲዎችና ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጆች ማህበር (ATUPA) ዋና ጸሀፊ ከሆኑት ዶ/ር ጃሁ ሳምባ ጋር ተወያይተዋል።
የአፍሪካ መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ የዚህ ፓን አፍሪካዊ ተቋም አባል ሳትሆን መቆየቷ እንደሚያስቆጫቸው የገለጹት ዋና ጸሃፊዋ ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስክ እንዳለ መሪ ተቋም በአባልነት ቢቀላቀል በርካታ ዘርፉን የሚለውጡ ተግባራት እንደሚሰራ እምነታቸውን አንስተዋል።
አፍሪካ ወጥ የሆነ ስርዓተ ስልጠና ያስፈልጋታል ያሉት ዶ/ር ጃሁ ይህንንም ለማሳካት እንደ ኢንስቲትዩቱ ያሉ ተቋማትን ማስተሳሰር ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ክህሎት ማህበር አባል መሆኗን፣ ኢንስቲትዩት ለዓለም አቀፍ ገበያ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት ተልዕኮ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ፣ ከአገር አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት ዜጎችን እያሠለጠነ እንደሚገኝ፣ የገለጹት የኢንስቲትዩቱ የስልጠናና አቅም ግንባታ ም/ዋና ዳይሬክተር ሐፍቶም ገ/እግዚአብሄር (ረ/ፕሮፌሰር) የዚህ ማህበር አባል መሆን ተልዕኮውን ለማሳካት ያስችለዋል ብለዋል።
በቀጣይ ዝርዝር ውይይት ተደርጎ እንደሚወሰንም ም/ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ማህበሩ በጋና አክራ በ1997 እ.አ.አ የተቋቋመ እና በአሁኑ ጊዜ መቀመጫውን በናይሮቢ ኬኒያ ያደረገ ፓን-አፍሪካዊው ተቋም እንደሆነ ተገልጿል።