ዓለምአቀፍ በያጆችን በስፋት እና በጥራት ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር ገለጹ። ************ህዳር 1/2017**********

በኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ማምረትና ብየዳ ልህቀት ማዕከል በዓለምአቀፍ ብየዳ የአሰልጣኞች ስልጠና የተከታተሉ ሠልጣኞች ተመርቀዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር በምረቃ ሥነስርዓት ላይ እንደገለጹት የብየዳ ሙያ በአገራችን እያደገ በመጣው በማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ እና በመላው ዓለም ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ በዘርፉ ብቁ ሙያተኞችን በስፋት ለማፍራት ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለተለያዩ ኢንደስትሪዎች ብቁ የብየዳ ሙያተኞችን እያቀረበ እንደሚገኝ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ማዕከሉ የተሠጠውን አገራዊ ራዕይ፣ ያለውን የሠለጠነ የሰው ሐይል እና የተደራጀ የስልጠና ወርክሾፕ በማስተሳሰር የዌልዲንግ ሙያን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የብየዳ ስልጠናን ዘመኑ ከደረሰበት ስማርት ዌልዲንግ አኳያ ለማስተሳሰር ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ብሩክ ለኢንደስትሪዎች እና ለክልል ሙያተኞች ቀጣይነት ባለው መልኩ ይሰጣል ብለዋል።
የቴክኖሎጂ ማምረትና ብየዳ ልህቀት ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶ/ር ሠላሙ ይስሀቅ በበኩላቸው ይህ በ2017 ዓ/ም የመጀመሪያ ዙር ዓለምአቀፍ ብየዳ የአሰልጣኞች ስልጠና በሞጁል አንድ እና ሁለት ለ40 ቀናት የተሰጠው ስልጠና የንድፈሐሳብ እና የተግባር ስልጠናን ያካተተ ከመሆኑም በተጨማሪ አስፈላጊው ምዘና እንደተካሄደ ገልጸዋል።
ምዘናውን ያለፉ ሠልጣኞች ዓለምአቀፍ የፊሌት ዌልደርነት ሰርተፊኬት ከዋና ዳይሬክተሩ እጅ ተቀብለዋል።