ኢንስቲትዩቱ በ2017 ለሀገር ውስጥና ለዓለምአቀፍ ገበያ ብቁ የሆኑ በያጆችን በስፋት እና በጥራት ለማፍራት እየሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ። ******መስከረም 28/2017********

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የ2017 ዓ/ም የዓለምአቀፍ ብየዳ የአሰልጣኞች ስልጠናን በይፋ አስጀምሯል።
የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ማምረትና የብየዳ ልህቀት ማዕከል ሐላፊ የሆኑት ዶ/ር ሠላሙ ይስሐቅ ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት ማዕከሉ ከዓለምአቀፍ የብየዳ ኢንስቲትዩት ዓለምአቀፍ በያጆችን አሠልጥኖ ዓለምአቀፍ ደረጃ ያለው ሰርተፊኬት መስጠት የሚችል ተቋም መሆኑን እና ለአገራችን ገበያ ብቁ በያጆችን ሲያፈራ የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ማዕከሉን በሙሉ አቅሙ ወደስራ እንዲገባ በማድረግ በ2017 ዓ/ም ከሀገር አልፎ ለዓለምአቀፍ ገበያው ፍላጎት ብቁ የሆኑ ዓለምአቀፍ በያጆችን በስፋት ለማፍራት እንደሚሠራም ዶ/ር ሠላሙ አብራርተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ የአገራችን ክፍል ለተውጣጡ 120 ለሚሆኑ አሠልጣኞች በሦስት ዙር የአሠልጣኞች ስልጠና እንደሚሠጥ የገለጹት ሀላፊው እያንዳንዱ ዙር አንድ ወር ከአስር ቀናት እንደሚፈጅ እና ዘጠና በመቶ የተግባር አስር በመቶ ደግሞ የንድፈሐሳብ ስልጠናዎችን እንዳካተተ ተናግረዋል።
የማዕከሉ የዓለምአቀፍ ብየዳ ስልጠና መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ሙሉቀን ዓለሙ በበኩላቸው ማዕከሉ ዌልደርና ሱፐር ቫይዘር እንደሚያፈራ ገልጸው ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና የመጀመሪያ ደረጃ የፊሌት ዌልዲንግ ደረጃ ዲፕሎማ የሚያስገኝ እንደሆነ ተናግረዋል። ስልጠናው በMIG/Mag, TIG and MAM proces በሞጁል አንድናሁለት እንደሚሰጥ ጨምረው ገልጸዋል።
የብየዳ ብቃት ምዘና እና የሠርተፊኬሽን መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ፋንታሁን በበኩላቸው ስልጠናቸውን ጨርሰው ወደገበያው የሚወጡ በያጆች ብቃታቸውን ለማረጋገጥ ጥብቅ ምዘና እንደሚከናወን ገልጸዋል።