ኢንስቲትዩቱ ለመሀል ሜዳ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ 10 ሚሊየን ብር የሚገመቱ የሥልጠና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ። ************መስከረም 27/2017**********

የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀብታሙ ሙሉጌታ ለመሀል ሜዳ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ ግምታቸው 10 ሚሊየን ብር የሆኑ የስልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ለተለያዩ ትምህርት ክፍሎች እና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን አስረክበዋል።
ዶ/ር ሐብታሙ በርክክቡ ሠአት እንደገለጹት ኢንስቲትዩቱ የስልጠና ተቋማትን ለመደገፍ የስልጠና ጥራትን የሚያሳድጉ የቁሳቁሶችን፣ የአቅም ግንባታ እና መሠል ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
መሐል ሜዳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በደረሰበት ጉዳት ስልጠና ለመስጠት መቸገሩን የጠቀሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ይህ ድጋፍ ተቋሙን ወደ ስልጠና ስራ እንዲመለስ ያስችለዋል ብለዋል።
የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ ዲን አቶ ኢዩኤል አስፋው በበኩላቸው ኮሌጁ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ውድመት የደረሰበት በመሆኑ፣ ከዚህም በተጨማሪም በዚህ ዓመት ወደ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በማደጉ ሰፊ የሆነ ግብአት ፍላጎት እንዳለው አንስተዋል። ለዚህም ኢንስቲትዩቱ ያደረገላቸው ድጋፍ ለስልጠና ጥራት የሚኖረው አበርክቶ ላቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
ድጋፍ ከተደረጉት የስልጠና ቁሳቁሶች መካከል ኤሌክትሮኒክ ትሬኒንግ ቦርዶች፣ ፕሮጀክተሮች ፣ ፎቶ ኮፒ ማሽን ፣ በርካታ ኮምፒውተሮች ፣ ተሽከርካሪ ሞተር ሳይክል፣ ኤሌክትሪካል የልብስ ስፌት ማሽኖች እንዲሁም የተለያዩ አይነት ማሰልጠኛ ማሽኖች እና የቢሮ ወንበርና ጠረጴዛዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል።