አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016 (ኢዜአ):-በቴክኖሎጂ ፈጠራ ተወዳድረው ያሸነፉ ወጣቶች የፋብሪካ ማሽነሪን ጨምሮ ችግር ፈች የምርምር ውጤቶችን ማፍለቅ መጀመራቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰመር ካምፕ ቴክኖሎጂ ኤክስፖን ጎብኝተዋል።

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2016 (ኢዜአ):-በቴክኖሎጂ ፈጠራ ተወዳድረው ያሸነፉ ወጣቶች የፋብሪካ ማሽነሪን ጨምሮ ችግር ፈች የምርምር ውጤቶችን ማፍለቅ መጀመራቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰመር ካምፕ ቴክኖሎጂ ኤክስፖን ጎብኝተዋል።
በኤክስፖው በፈጠራ ስራ ተወዳድረው ያሸነፉ ወጣቶች ባለፉት አንድ ዓመት በሰመር ካምፕ ሆነው ያሻሸሏቸውን የቴክኖሎጂ ስራዎች አቅርበዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት መመሪያ መሰረት የፈጠራ ባለሙያዎች ከምስለ ምርት ባሻገር ተኪ ምርቶችን ማምረት ጀምረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በፈጠራ ሀሳብ፣ በክህሎትና ቴክኖሎጂ ማበልጸግ ተወዳድረው ያሸነፉ 400 የአሸናፊዎች አሸናፊ ወጣቶች ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ምስለ ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር እና በማሻሻል ለገበያ ያቀረቡ ወጣቶችን ወደ ሚቀጥለው ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት በ11 ዘርፎች 81 ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ እንደተቻለ የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ለ45 ቴክኖሎጂዎች የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ጥበቃ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የመካከለኛና ከፍተኛ ኩባንያነት ራዕይ የሰነቁ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ሥራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞቹ ከተኪ ምርቶች ባለፈ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውንም አንስተዋል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የቴክኖሎጂ ፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ስምምነት መደረሱንም ገልጸዋል፡፡
በወጣቶች የሰመር ካምፕ የቴክኖሎጂ ፈጠራና እሴት የመደመርን ጉልበት በተግባር አይተናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በትብብር በመስራት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በመሻገር ቀን ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ ሽግግር መነሳት እንደሚገባ ጠቁመው እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶች ባለንበት እንድንኩራራ ሳይሆን በቀጣይም የተሻለ መስራት እንዳለብን የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል፡፡