የቴክኒክና ሙያ ስርዓት ለጥራት ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ። ******ሐምሌ 19/2016******
የኮርያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (KOIKA) ለፌደራልና ለክልል የቴክኒክና ሙያ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና አዘጋጅቷል። በስልጠናውም ኮርያ እና ኢትዮጵያ በቴክኒክና ሙያ ስርዓታቸው ውስጥ ልምድ የሚለዋወጡባቸው ጉዳዮች እየተነሱ ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር #ብሩክ_ከድር በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ስርዓት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ስርዓቱ እንደአገር ከተጀመረበትጊዜ ጀምሮ ያለውን ሒደት የሚያሳይ ሰነድ አቅርበዋል።
በሠነዳቸውም ተቋማዊ ጥራትን ለማረጋገጥ ልንከተላቸው ይገባሉ ያሏቸውን ሐሳቦች አንስተዋል። ስለስርዓተ-ስልጠና ጥራት፣ ብቃት ያላቸው አሠልጣኞችን፣ የተቋማቱ መሠረተልማት ጉዳይ፣ በዘርፉ ላይ የኢንደስትሪው በትብብር መቆም፣ ምዘናና ሰርተፊኬት፣ ተከታታይነት ያለው የጥራት ስራ ለዘርፉ የጥራት ስራ በትኩረትሊሰራባቸው ይገባል በሚል ካነሷቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
እንደአገር ለረጅም ጊዜ የዘርፉን ጥራት ለማስጠበቅ የወጡ የህግ ማዕቀፎችን የተሞከሩ ተግባራትንም ዳስሰዋል ። ዶ/ር ብሩክ በጽሁፋቸው በአሁኑ ጊዜ የየኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲውን ጨምሮ እየወጡ ያሉ ህጎች ለጥራት ልዩ ትኩረት ይዘው መስጠታቸውን ገልጸዋል። እንደአገር የቴክኒክናሙያ ስልጠና ተቋማት ጥራታቸው የተጠበቀ እንዲሆንና የጥራት ተሸላሚ እንዲሆኑ ሊሰሩ ይገባል ያሏቸውንም ሐሳቦች በሰነዳቸው አካትተው አቅርበዋል። ተወያዮችም ሰፊ ውይይት አሂደውበታል።
የኮርያ የቴክኒክና ሙያ ስርዓት ለጥራት በሠጠው ትኩረትና በተሠራ ያላሠለሠ ጥረት የመጡ ለውጦች ለልምድ ልውውጥ ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ለማወቅ ተችሏል።