የቋንቋና ባህል ትስስርን ማጎልበት ላይ ትኩረቱን ያደረገው የቻይና ቋንቋ ውድድር “ቻይኒዝ ብሪጅ” 23ኛው ዙር የኢትዮጵያ ውድድር በኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ግቢ ውስጥ ተካሂዷል። *****************ግንቦት 28/2016***********
በኢትዮጵያ የቻይና ቋንቋን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚያጠኑ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ይህ ውድድር በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት የሦስትዮሽ ትብብር የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል።
ቻይንኛን አንድ ክፍለ ጊዜ በሚወስዱ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ጨምሮ በድምሩ 11 ተማሪዎች በውድድሩ የተሳተፉ ሲሆን ተማሪዎቹ በቻይንኛ ቋንቋ ንግግሮች፣ የቻይንኛ ሙዚቃ፣ ስፖርት፣ የቻይና ባህል ላይ ያተኮሩ ጥያቄና መልስ እንዲሁም ሌሎች የመድረክ ሥራዎችን በማቅረብ ተወዳድረዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ በሥነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በበርካታ ዘርፍ እያደገ የመጣውን የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቋንቋ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያውያን የቻይንኛ ቋንቋ ማወቃቸውም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ከማጠናከሩም በተጨማሪ የሥራ አማራጮችን የሚያሰፋ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሺን ኪንሚን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የቻይንኛ ቋንቋ መሠጠት በሁለቱ አገራት መካከል የቆየውን የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያጠነክረዋል ብለዋል።