ኢንስቲትዩቱ የISO 9001:2015 የጥራት ተሸላሚ ለመሆን የጀመረው ስራ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ ***********ግንቦት 23/2016************

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የISO 9001:2015 የጥራት ተሸላሚ ለመሆን ከግንቦት 1/2016 ዓ/ም ጀምሮ በይፋ ያስጀመረው ስታንዳርዶችን የመፈጸም ስራ በጥሩ አፈጻጸም እንደሚገኝ ዋና ዳይሬተሩ ዶ/ር #ብሩክ_ከድር ገልጸዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ እንደመሪ ተቋም በሁሉም መስክ አርአያ ሆኖ ለመገኘት እየሰራ ነው ያሉት ዶ/ር ብሩክ ተግባራትን ሁሉ በጥራት ስታንዳርድ መተግበር ለዚህ አጋዥ መንገድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም ለዳይሬክተሮች እና ቡድን መሪዎች፣ ለፋካሊቲ ዲኖች እና ትምህርት ክፍል ሀላፊዎች፣ ለካምፓስ ፖሊስ አባላት ስልጠና እየተሰጠ ሲሆን ይህም የሆነው የኢንስቲትዩቱ ማህበረሰብ ተመሳሳይ ግንዛቤ እና የመፈጸም ቁርጥነት መያዝ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የጥራት ተሸላሚ ለመሆን በትኩረት በመያዝ ከ11ዱ የሪፎርም ሀሳቦች አንዱ በማድረግ ከተግባሩ ጋር ከጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ሙያተኞች የያዘ አስተግባሪ ቡድን ተዋቅሮ ሰፊ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የጠቀሱት ዶ/ር ብሩክ የጥራት ፖሊሲ እንደተዘጋጀ፤ ተቋማዊ አገልግሎት መስጫ መንገዶችን ወጥነት የማስያዝ ስራ እንደተሰራ፤ ከማኔጅመንት አባላት ጀምሮ ለሁሉም የኢንስቲትዩቱ ማህረሰብ አባላት ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ አካዳሚክ ጉዳዮች ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር #ሐፍቶም_ገብረ_እግዚአብሔር (ረ/ፕሮፌሰር) በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ለአገርአቀፍ እና ዓለምአቀፍ ገበያ ፍላጎት የሚመጥኑ ብቁ ሰልጣኞችን የማፍራት፣ ተኪ ቴክኖሎጂ የማምረት፣ ዓለምአቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ጥናትና ምርምር የማካሔድ ዕቅዳችን የሚሳካው ገበያው የሚፈልገውን ስታንዳርድ እስካሟላን ድረስ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በአንድነት ተባብረን የISO 9001:2015 ስታንዳርደችን በመፈፀም የጥራት ተሸላሚ መሆን አለብን ብለዋል፡፡