ሁዋዌ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የአይሲቲ ስልጠና ማዕከሉን አስጀመረ።

ሁዋዌ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የአይሲቲ ስልጠና ማዕከሉን (HUAWEI ICT Academy) አስጀመረ።

*********** *********

ሁዋዌ ዓለምአቀፍ የመረጃ እና የመገናኛ ቴክኖሎጂ (ICT) መሠረተ-ልማት አቅራቢና አገልግሎት ሰጪ ተቋም ሲሆን በቴክኖሎጂ ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የላቀ ክህሎትን የሚያስጨብጡ ስልጠናዎችን ከአንድ መቶ አስር በላይ ሐገራት ባሉ ከ1ሺህ ዘጠኝ መቶ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን እያሰለጠነ ሰርቲፊኬት እየሠጠ ይገኛል። ተቋሙ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የአይሲቲ ስልጠና ማዕከሉን ማስጀመሩን አስመልክቶ ሚያዚያ 19/2015 ዓ/ም ከተማሪዎች ጋር ውይይት አካሒዷል።

ወ/ሮ #ቤተልሔም_መስፍን የሉባን ወርክሾፕ ዳይሬክተር እና HUAWEI ICT Academy የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት አስተባባሪ ናቸው።

ኢንስቲትዩቱ በአይሲቲ ዳይሬክቶሬት በኩል ከሁዋዌ ጋር በሠራው ተከታታይ ግንኙነቶች የስልጠና አካዳሚ ማስጀመር ተችሏል ብለዋል። ተማሪዎች በኢንስቲትዩቱ ከሚሰጣቸው መደበኛ ስልጠና በተጨማሪ ክህሎት የሚጨብጡበት ሲሆን ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ኢንደስትሪውን በቀላሉ ለመቀላቀል የሚያግዝ ትልቅ እድል ነው በዚህም ከአገራችንም አልፈው በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳድረው ስራ የሚይዙበትን እድል ይፈጥራል በማለት ያለውን አበርክቶ ያስረዳሉ።

እንዲህ ያሉ ስልጠናዎች በአገራችን የቴሌኮም ዘርፍ ያሉ የሙያተኞች ፍላጎት እና አቅርቦትን የማጣጣም አገራዊ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

ሁዋዌ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና በመስጠት በብቃት ለሚያጠናቅቁ ዓለምአቀፍ እውቅና ይሰጣል። ይህም ተማሪዎች ዘመናዊውን ዓለም እንዲተዋወቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል።

አቶ #እንዳለ_ለገሰ በሁዋዌ ኢትዮጵያ የአይሲቲ ታለንት ኢኮ ሲስተም ማናጀር ሲሆኑ ሁዋዌ ከሚሰራቸው ዘርፈብዙ ተግባራት መካከል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአይሲቲ ስልጠና ማዕከል በመክፈት ስልጠና እየሠጠ ይገኛል። ከስልጠና በኋላም በድርጅቱ ላይ የስራ እድል እንዲያገኙ፣ ከቀጣሪዎች ጋር እንዲገናኙ ያመቻቻል። ይህ ለኢንስቲትዩቱ ተማሪዎች ትልቅ እድል ነው ብለዋል።

ሁዋዌ በአገራችን ከአርባ ሦስት በላይ ዩኒቨርስቲዎች ጋር እየሠra ሲሆን ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር መስራቱ ለየት የሚያደርገው ኢንስቲትዩቱ ቴክኒካል ስልጠና የሚሰጥ በመሆኑ ከሁዋዌ የቴክኒካል ስልጠናዎች ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።

ተማሪ ሰመረ መኮንን ኢንስቲትዩቱ ከሁዋዌ ጋር በቅንጅት ለመስራት የጀመሩት ይህ የአይሲቲ ስልጠና ማዕከል ዘመናዊው ዓለም የፈጠረውን እድል የመጠቀም ምቹ መደላድል ይፈጥርልናል ብሏል፡፡ የመጣልንን እድል በአግባቡ መጠቀም ከቻልን ለወደፊቱ የስራ እድል ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን። ጊዜው የቴክኖሎጂ ነው ጊዜው የፈጠረልንን እድል በመጠቀም ተጠቃሚ የምንሆንበትን ምቹ ሁኔታ ይዞልን በመምጣቱ ደስተኞች ነን ብሏል።

የስልጠና አሰጣጡ የገጽለገጽ እና የonline አማራጭ ስላለው ሰልጣኞች በሚፈልጉት አማራጭ ራሳቸውን ማብቃት ይችላሉ ተብሏል።