የሴት መምህራን ፎረም የምስረታ ጉባኤ ተካሔደ፡፡

Federal TVET Institute

October 29, 2019

በፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት የሴት መምህራን ፎረም የምስረታ ጉባኤ የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ሴት መምህራን በተገኙበት ተካሔደ፡፡

በምስረታ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የአካዳሚክ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሀብቶም ገ/እግዚአብሔር እንደገለፁት ‹‹የሴት መምህራን ፎረም ሲመሰረት መብትን ከማስከበር ባለፈ ሴቶች ለተቋማዊ ለውጥ ያላቸው ድርሻ ላቅ ያለ መሆኑን ለማገንዘብ እና ለማነሳሳት መሆን አለበት›› ብለዋል፡፡

የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ አመለወርቅ ክፍሌ የፎረም ስራአስፈጻሚ አባላትን ባስመረጡበት ወቅት በሀገራችን የተገኘው ውጤት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የውጤቱ ተጠቃሚ የሆኑት ሴቶች ጉዳዩን ከመንግስት መዋቅሮች በተጨማሪ በባለቤትነት ይዘው ለተሻለ እድገትና የፆታ እኩልነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በትምህርት ተቋማት ውስጥ የሴቶች የአመራርነት ተሳትፎ ለውጡና ተግዳሮቶቹ ላይ የሚያተኩር ጥናት እየተካሔደ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

ተሳታፊ ሴት መምህራንም በፎረሙ መመስረት ደስታቸውን ገልፀው ይህ ፎረም ሴቶች ከወንዶች የሚወዳደሩበት ሳይሆን አብረው ሆነው ለለውጥ የሚሰሩበት እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ ሴት መምህራን ላይ የእኔነት ስሜት አለመኖር፣ ሴቶች በራሳቸውም ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ አለመሆን፣ በኢንስቲትዩቱ በኩል መሟላት ያለባቸው እንደ የህጻናት መዋያ ያሉ አለመዘጋጀታቸው እና ሌሎችም ክፍተቶች ያሉ ሲሆን እነዚህን ችግሮች ከአመራሩ ጋር በመሆን ለመፍታት ይሰራል ተብሏል፡፡

ሴት የአስተዳደር ሰራተኞች ፎረም ቀደም ብሎ እንደተዘጋጀ እና በቀጣይ የሴት ተማሪዎች ፎረም እንደሚመሰረት ወ/ሮ አመለወርቅ ተናግረዋል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti