የጀርመን መንግስት ከፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍን ለማሳደግ የሚያስችል የስምምነት ተፈራረሙ፡፡

Federal TVET Institute

ጥቅምት14/2012

በጀርመን በምክትል ጠቅላይ ሚንስት ማዕረግ የሔሰን ፋይናንስ ሚንስትር ታዜር አልዋዚር የመሩት እና ከንግድ ምክርቤት ከኮሌጆች እና ከመንግስት ከፍተኛ ኃለፊዎች የተውጣጡ ከሰላሳ አምስት በላይ አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ቆይታው በፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት በመገኘት አብሮ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴርን በመወከል የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ የልዕካን ቡድኑን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ በዚሁም ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካለቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ጥረት ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናን የትኩረት መስክ አድርጋ እየሰራች እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡

‹‹የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በአገራችን አሁንም ውስንነቶች ያሉበት ቢሆንም GIZ እና KFWን ከመሳሰሉ የጀርመን ድርጅቶች ጋር እየተደረገ ባለው ትብብር ዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥቷል›› ብለዋል፡፡

አቶ ጌታቸው አያይዘውም የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩ ሲሆን‹‹ የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚመሩ የቴክክና ሙያ አመራሮችን፣ ቴክኖሎጂዎችን የሚቀዱና የሚያፈልቁ መምህራንን ለማፍራት በመንግስት በትኩረት እየተደገፈ ያለ ኢንስቲትዩት ነው ብለዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑን የመሩት ሚንስትሩ ታዜር አልዋዚር በበኩላቸው በጀርመን ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንድ ሦስተኛ ያህሉ በእሳቸው ግዛት (ስቴት) በሔሰን የሚገኙ መሆኑን በማውሳት በኢትዮጵያ ለመገኘት አንዱ አነሳሽ ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡

በፖለቲካና ኢኮኖሚ ለውጥ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶቿን ስራ ለማስያዝ የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ማጠናከር ብቸኛ አማራጯ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የሀገራቸውን ተሞክሮ ጭምር በመጥቀስ::
ኢትዮጵያ እና የጀርመኗ ሔሰን ግዛት የቆየ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ሁለቱም መሬት እና የሰው ሀይል ብቸኛ ሀብታቸው መሆኑ እንደሚያመሳስላቸው የተናገሩት ደግሞ የGIZ ተወካዩ ሚስተር ሆረስት ናቸው፡፡ ሚስተር ሆረስት እንደተናገሩት የተደረገው የትብብር ስምምነት በዋናነት የመምህራንን ጥራት ማሻሻል፣ የመምህራንን ቁጥር መጨመር እና በትብብር ስልጠና ክፍተቶችን መሙላት ላይ ያተኩራል፡፡

የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በሬቻ የሀገራችንን የቴክኒክና ሙያ እድገት በተለይም የኢንስቲትዩቱን የለውጥ ጉዞ የሚያስረዳ ጽሑፍ ካቀረቡ በኋላ ልዑካኑ በጀርመን ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ የተደራጁትን የስልጠና ክፍሎች ጎብኝተዋል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti