ኢትዮጵያና ስሎቫክ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ አብረው ለመስራት እንደሚፈልጉ የስሎቫክ ሪፑብሊክ አምባሳደር ገለፁ፡፡

Federal TVET Institute

October 17, 2019

የስሎቫክ አምባሳደር ክቡር ድራሆሚር ሽቶስ ዛሬ በፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት አምባሳደሩ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ እያካሔደች ያለውን ስሎቫክ ታደንቃለች፡፡

ለአገሪቱ ለውጥ ትምህርት ያለውን ከፍተኛ ሚና ያስታወሱት አምባሳደር ሽቶስ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች አቅም ለማሳደግ ኢንስቲትዩቱ በሚያደርገው ጥረት ከጎናችሁ እንቆማለን ብለዋል፡፡

በተለይም በስሎቫክ ሪፑብሊክ የሚገኘው የዙለን ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ለፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አሰልጣኞችና ቴክኒሺያኖች ከፍተኛ ልምድ ሊያጋራ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በሬቻ እንዳሉት የአውሮፓዊቷ አገር አምባሳደር ጉብኝት ቀጣይ ኢንስቲትዩቱን ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል፡፡

በቅርቡ በቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ስራውን ለሚቀጥለው ኢንስቲትዩቱ መምህራንን በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ለማሰልጠን፣ የቴክኒክና የአመራር እንዲሁም የአደረጃጀት ልምድ ለመቅሰም ስሎቫክ ምቹ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሏት አምባሳደሩ መግለጻቸውን አቶ ተሻለ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሩ የውድወርክ የስልጠና ክፍልን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ ሞቲ ነብዩ እንዳሉት ትምህርት ክፍሉ ከፍተኛ የሆነ በመስኩ የሰለጠነ የሦስተኛና የሁለተኛ ዲግሪ መምህራን እጥረት መኖሩን አስገንዝበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የስሎቫክ ሪፑብሊክ ኤምባሲ እና ኢንስቲትዩቱ በቅርቡ የጋራ ስምምነት ሰነድ የሚፈራረሙ ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሁለቱ ሀገራት በትብብር እንደሚሰሩ ክቡር አምባሳደር ድራሆሚር ሽቶስ ገልፀዋል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti