የግብርና ኮሌጆች ብቁ የሰው ሀይል ለማፍራት እየሰራን ነው አሉ፡፡

Federal TVET Institute

መስከረም 15/2012-ቢሾፍቱ

በኢትዮጵያውያን እና በውጭ ባለሀብቶች የሚንቀሳቀሱ በቁጥር የበዙ በግብርናው ዘርፍ ላይ አትኩረው የሚሰሩ የግል ድርጅቶች /companies/ በሀገራችን ቢኖሩም ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በትስስር ስለማይሰሩ በዘርፉ የተማረ የሰው ሀይል ለማፍራት ሚናቸው አናሳ ሆኖ ይታያል፡፡

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀዉ የሚወጡ ተማሪዎች ስልጠናቸው ንድፈሀሳብ የበዛው በመሆኑ በባለሙያነት ከተቀጠሩ በኋላ ተጨማሪ ስልጠና መስጠት እንደሚገደዱ ድርጅቶቹ ያስረዳሉ፡፡ 

በ Bright Future in Agriculture ፕሮጀክት የሚደገፉ ስድስት የግብርና ኮሌጆች በቢሾፍቱ ከተማ ባካሔዱት የመስክ ጉብኝት እና ውይይት ከካምፓኒዎች ጋር በትብብር ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

ጉብኝት ከተካሔደባቸው ድርጅቶች መካከል ጆይቴክ ኃ.የተ.የግ. ኩባንያ አንዱ ሲሆን የግብርና ስራአስኪያጁ አቶ ብስራት ኃ/ስላሴ እንደሚሉት ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች ተማሪዎቻቸውን ወደ ድርጅታቸው በማምጣት ስልጠና ያሰጣሉ፡፡ በተግባር ተሽለው የተገኙትንም እንደሚቀጥሩ ይናገራሉ፡፡ 

ይሁንና ተማሪዎቹ በእርሻ ቦታዎች እየተገኙ ተከታታይ ስልጠናዎችን በተግባር ስለማይወስዱ የክህሎት ክፍተት ያለባቸው መሆኑን እንደታዘቡ አቶ ብስራት ያስረዳሉ፡፡ 

በወረታ ግብርና ኮሌጅ የባዮ ቴክኖሎጂ መምህር የሆኑት ጥላሁን ጌቱ የአቶ ብስራትን ኃሳብ ያጠናከራሉ፡፡ ኮሌጁ ከማስተማር ባለፈ ህረተሰቡን የሚጠቅም ስራ ለመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑን በዚህም የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬ ዝርያዎች በማላመድ ለአርሶ አደሩ ማቅረባቸውን ይገልፁና ‹‹ዘርፉ የሚጠይቀው ግብአት ከፍተኛ ገንዘብ በመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ ማሟላት አልተቻለም፤ ይህ ደግሞ ተማሪዎች በቂ ልምምድ እንዳያደርጉ እንቅፋት ሆኗል›› ይላል፡፡
ኮሌጆች ከካምፓኒዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ለዘርፉ የሚያግዙ ብቁ ሰልጣኞችን ለማፍራት በቀጣይ ተባብረው እንደሚሰሩ በመስክ ጉብኝቱ ወቅት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ 

የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ከኔዘርላንድስ መንግስት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት የሚስችል ፕሮጀክት( Bright Future in Agriculture) እየተገበረ ይገኛል፡፡ 

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti