የአርባምንጭ ፖሊ-ቴክኒክና ሳተላይት ኮሌጅ ለ21ኛ ጊዜ ሰልጣኞችን አስመረቀ፡፡

Federal TVET Institute

ነሀሴ 20/2011

የአርባምንጭ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ እና የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ሳተላይት ተቋም ከደረጃ 2-5 እንዲሁም በዲግሪ መርሀግብር ሲያሰለጥኗቸው የነበሩ 1291 ሰልጣኞችን ነሀሴ 18/2011ዓ/ም አስመርቀዋል፡፡ 
የአርባምንጭ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ በደረጃ ሲያስመርቅ ይህ 21ኛ ጊዜ ሲሆን ይህ ምረቃ ለየት የሚደርገው ከፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በዲግሪ ደረጃ ሲያስመርቅ የመጀመሪያ ጊዜው በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት በኮሌጁ የከፈተው ሳተላይት ተቋም በማኑፋክቸሪንግ እና በጋርመንት ትምህርት ክፍሎች ሲሆን በድምሩ 37 ሰልጣኞችን ሲያሰለጥን ቆይቶ ለምረቃ አብቅቷል፡፡
የኮሌጁ ዲን የሆኑት አቶ በዛብህ ባርዛ በእለቱ መልዕክታቸው እንደገለፁት ኢንስቲትዩቱና ኮሌጁ የአካባውን ብሎም የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ መሰረት አድርገው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህ የተነሳ እስካሁን ከኮሌጁ የተመረቁ ሙያተኞች በየስራ ዘርፋው ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የጋሞ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪ እና የኮሌጁ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ብርሀኑ ዘውዴ በበኩላቸው አካባቢው የበርካታ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው ተመራቂዎች ተቀጥሮ የመስራት ሀሳብን ወደጎን በማለት በራሳቸው ስራ ፈጥረው ቢሰሩ ከዚህ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ራሳቸውንም አካባያቸውንም እንደሚጠቅሙ ተናግረዋል፡፡
የሳተላይት ፕሮግራሙ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ይልማ ጥላሁን ሳተላይት ተቋማትን በክልሎች መክፈት የመጀመሪያ ዲግሪ (B level) አሰልጣኞችን ቁጥር ለማሳደግ፣ በሌቭል የተመረቁ ተማሪዎችም ራሳቸውን የማሻሻል ተነሳሽነት እንዲፈጥሩ ሁሉም ሰው በአካባቢው የመማር እድል እንዲያገኝ ለማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህም የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ይህንን በማድረጉ ወሳኝ ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
ከሳተላይት ተቋሙ ተመራቂዎች ከማኑፋክቸሪንግ ትምህርት ክፍል የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ተስፋዬ ተሰማ አሁን ያለበት ደረጃ ጅምር መሆኑን ገልፆ ለቀጣይ የትምህርት ደረጃዎች እንዳነሳሳው ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም እስካሁን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የሰራ ሲሆን በቀጣይም ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለመስራት አቅሙን አሟጦ እንደሚጠቀም ተናግሯል፡፡
ሳተላይት ተቋሙ በቀጣይ ወደ አምስት የትምህርት ክፍሎች በማሳደግ ለማስተማር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የኮሌጁ ዲን አቶ በዛብህ ባርዛ ተናግረዋል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti