የዲጂታል ትምህርት (Digital Content) ዝግጅት ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ወሳኝ ነው ተባለ፡፡

Federal TVET Institute

ሰኔ 10/2012

የገጽ-ለገጽ ትምህርትን ለማስኬድ አስቻይ ሁኔታዎች በማይፈጠሩበት ጊዜ የተለያዩ ማስተማሪያ ጽሑፎችን፣ ቪዲዮዎችን፣ የድምጽ ቅጅዎችን እና ሌሎችንም ማስተማሪያዎች በአንድ ድረ-ገጽ ላይ በተዘጋጀ ቋት በማስቀመጥ (Digital Content በማዘጋጀት) ማስተማር ወሳኝ ተግባር ነው፡፡

ዛሬም ዓለማችን በተፈጠረበት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በሀገራችን የገጽ-ለገጽ ትምህርት ከተቋረጠ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ተማሪዎች በቤታቸው ሆነው መማር እንዲችሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት Digital Content እንዲያዘጋጁ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ሚንስቴር መ/ቤቱም ባዘጋጀው http://ndl.ethernet.edu.et ድህረ-ገጽ ወደ ሰማኒያ ሺህ የሚጠጉ ማስተማሪያ ሰነዶችን አስቀምጧል፡፡

የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩትም ባለፈው ዓመት የጀመረው የe-learning platform አሻሽሎና አዘምኖ ቀጥሎበታል፡፡

አብዛኛውም መምህራንም በተዘጋጀላቸው ቋት ላይ ሰነዶችን እየጫኑ ለተማሪዎቻቸው እያዘጋጁ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና ሁሉም መምህራን ተመሳሳይ ክህሎት ይዘው እንዲሰሩ በማስፈለጉ በgoogle meet መተግበሪያ የታገዘ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡

ስልጠናውን የኢንስቲትዩቱ አይሲቲ ዳይሬክቶሬት ሲያዘጋጀው በጀርመን አገር ለረጅም ዓመታት e-learning ላይ የሰሩትና በአሁኑ ጊዜ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ብርሀኑ በየነ ስልጠናውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተደራሽነት ላይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፤ ይሁንና ያለ አይሲቲ ቴክኖሎጂ ይሳካል ማለት የማይታለም ነው፡ ይህንንም የተረዳው ኢንስቲትዩታችን የአይሲቲ ፖሊሲ (ICT Policy) እንዲኖረን እየሰራን ነው፡፡ ለዚህም ከፊንላንድ መንግስት ድጋፍ አግኝተናል›› ያሉት የኢንስቲትዩቱ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብቶም ገብረእግዚአብሔር ናቸው፡፡

ይህንንም ለማሳካት ከኢንስቲትዩቱ መምህራን በተጨማሪ በቀጣይ ለሳተላይት ተቋማትና ለፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኞች ስልጠናውን ለመስጠት እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡
ተማሪዎች በአጋጠመው ወቅታዊ ችግር ምክንያት ቤታቸው ቢቀመጡም ከትምህርት መራቅ የለባቸውም ያሉት አቶ ሀብቶም ተማሪዎች እንደዚህ አይነት ስርዓቶች (system) ጋር ራሳቸውን ማላመድ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ም/ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ኮቪድ-19 ወረርሽኝን መቋቋም ከቻልን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ በመንግስት በሚሰጥ አቅጣጫ መሰረት ተማሪዎች ወደ ገጽለ-ገጽ ትምርት ሲመለሱ ለሚሰጠው ትምህርት ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል ብለዋል፡፡

በአጠቃቀሙ ላይ በዝርዝር ስልጠና የተሰጠበት ይህ e-learning platform መምራን ሰነዶቻቸውን ከማስቀመጥ ባለፈ መምህራን ከተማሪዎች፣ ተማሪዎች ከተማሪዎች ጋር መወያየት እንዲችሉበት ተደርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ ሁሉም ተማሪዎች በተሰጣቸው ኮድ በመግባት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti