የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመከላከል ጎንለጎን የአረንጓዴ አሻራ ኃላፊነትን ለመወጣት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

Federal TVET Institute

June 15, 2020

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ በመገኘት የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የአረንጓዴ አሻራ ቀንን አስጀምረዋል።

ዶ/ር ሙሉ ችግኝ መትከልና መንከባከብ ከአንድ አገር ወዳድ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ገልጸው ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመከላከል ጎንለጎን ችግኝ በመትከል በኢትዮጵያ ምድር ላይ የአረንጓዴ አሻራቸውን ማስቀመጥ ይገባቸዋል ብለዋል።

አያይዘውም የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ማህበረሰቡ በቁጥሩ ከፍ ያለ እንደመሆኑ እያንዳንዳቸው 10 ችግኞችን መትከል ቢችሉ እንኳን በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከልና አገራችንን አረንጓዴ በማልበስ መርሃግብር ላይ አሻራቸውን ጥለው ማለፍ እንደሚችሉ ገልጸው ለተግባራዊነቱ እንዲሰሩም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ እንዳሉት የዩኒቨርስቲው የግብርና ኮሌጅ 70 ሺህ አገር በቀል ችግኞችን አባዝቶ ማዘጋጀቱንና በዚህም 50 ሺው ለከተማ አስተዳድሩ የተበረከተ መሆኑን ገልጸው የተቀረው ደግሞ በዩኒቨርስቲው አስተባባሪነት የሚተከል ይሆናል ብለዋል።

ዶ/ር ሙሉ የዩኒቨርስቲውን የስራ እንቅስቃሴ የጎበኙ ሲሆን የአፈር ምርምር ማዕከሉ በተለይ ለግብርናው ውጤታማነት የሚኖረው አስተዋጽኦ የላቀ እንደመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። በዩኒቨርስቲው የምርምር ማዕከል የተሰሩ ሳኒታይዘሮችን፣ በተፈጥሮ ግብዓት የተመረቱ ሽቶ የእጅና የመጸዳጃ ቤት ሳሙናዎችን ምርቶች ገብኝተዋል። የምርምር ውጤቶቹን በስፋት ወደ ምርት ለማስገባት እንዲቻል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።

ዩኒቨርስቲው ባለፈው ሳምንት የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም ያካሄደ ሲሆን በዛሬው ዝግጅት የደም ልገሳ ፕሮግራምም ተካሂዷል።
(MoSHE)

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti