ተማሪዎችን በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በክህሎት እና በአመለካከት የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ ነው፡፡

Federal TVET Institute

February 13, 2020

ሐገራችን ኢትዮጵያ ባላት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰውሀይል እና እያደገ በመጣው መሰረተ ልማት ሳቢያ የተለያዩ የዓለማችን ታላላቅ የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራች ኢንደስትሪዎች ለመሳተፍ ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ ይታያል፡፡ ባለፉት ዓመታትም ዘርፉ በአገራችን ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ይሁንና ኢንደስትሪው ያለው የሰው ሀይል እውቀት እና ክህሎት እንዲሁም የቴክኒክና ስራ አመራር ብቃት ማነስ ትልቅ የዘርፉ ማነቆ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ የማምረቻ መሳሪያዎች ኋላቀር መሆንም ሌላው እንቅፋት ነው፡፡

በዘመናዊ የማምረቻ እና የማሰልጠኛ ቁሳቁሶች የተደራጀው የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ዘመኑን የሚመጥን የጨርቃጨርቅና አልባሳት ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በተቋሙ ካሉት ተማሪዎች በተጨማሪ በሀገሪቱ ካሉ ከአስር በላይ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመጡ ተማሪዎችንም የተግባር ስልጠና ይሰጣል፡፡

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ 3ኛ ዓመት textile engineering ተማሪዎች በኢንስቲትዩቱ በመገኘት የተግር ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡
‹‹በፋብሪካዎች ስራ ላይ ብንሰማራ ልንሰራባቸው የምንችላቸውን ማሽኖች እና የምንሰራውን ስራ በዚህ ኢንስቲትዩት አግኝተናል፡፡›› ይላል በሦስት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታው ለሦስተኛ ጊዜ በመምጣት የተግባር ስልጠና እየሰለጠነ ያገኘነው ተማሪ ታምራት ደምሴ፡፡ ያካባተውን የንድፈ-ሀሳብ እውቀት ወደ ተግባር ለመለወጥ ስልጠናው እያገዘው እንደሆነ ያስረዳል፡፡

ሌላኛዋ ተማሪ ቤዛዊት ሠሎሞን አስፈላጊ የምርት እና የስልጠና ማሽኖች ተሟልተው ማግኘቷ እንዳስደሰታት ገልጻ እስካሁን በማሽኖቹ እያመረቱ መሰልጠን ባለመጀመራቸው በቀጣይ ቀናት የማምረት ስልጠና ቢሰጥ የበለጠ ጥሩ እንደሚሆን አስተያየቷን ሰጥታናለች፡፡

አቶ እሸቱ ሠሎሞን የ Apparel Fashion and Textile Technology ፋከለቲ ም/ዲን እና መምህር ናቸው ‹‹የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይዘውት የሚመጡትን የንድፈ-ሀሳብ እውቀት ወደተግባር ለመቀየር የሚያስችል ክህሎታቸውን የሚያዳብር ስልጠና እየሰጠናቸው እንገኛለን›› ይላሉ፡፡

የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በሀገራችን ብዙ ሊሰራበት የሚችል ቢሆንም ብዙ ያልተሰራበት በመሆኑ የማበረታታት ስራ ከዚህም በተጨማሪ የአመለካከት ግንባታም ጭምር እየሰሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡

‹‹እነዚህ ተማሪዎች ያላቸው የስልጠና ጊዜ አጭር ቢሆንም በዚህ ጊዜ የተሟላ እውቀት እንዲይዙ መምህራን የምሳ ሰዓታቸውን እና ከስራም በኋላ የእረፍት ሰዓታቸውን ሰውተው እያሰለጠኑ እንደሚገኙ አቶ እሸቱ የመምራንን ቁርጠኝነት ይናገራሉ፡፡
አቶ እሸቱ አያይዘውም ኢንስቲትዩቱ በፈጠረው የኢንዱስትሪ ቁርኝት ተማሪዎችን ወደ ፋብሪካዎች በመውሰድ የማምረት ስራ እየሰሩ እንዲሰለጥኑ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti