ኢትዮጵያ ለግብርና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚሆኑ ከሰላሳ በላይ ትራክተሮችና ማሽነሪዎች ድጋፍ ከጀርመን መንግስት አገኘች፡፡

Federal TVET Institute

December 3, 2019

በኢትዮጵያ እና በጀርመን መካከል በትምህርት መስክ ያለው ትብብር ከአርባ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ጀርመን ለኢትዮጵያዊያን እስከ 3ኛ ዲግሪ የሚደርስ የትምህርት እድል በመስጠት እያስተማረች ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው የጀርመን ፕሮፌሰሮችም በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡

ሀገራችንም ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናን በአዲስ መልክ ስታዋቅር ሞዴል ያደረገችውም የጀርመንን የትምህርት ስርዓት ነው፡፡

ይህንኑ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክር የትራክተሮች እና ማሽነሪዎች ድጋፍ ርክክብ በፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት ቅጥር ግቢ ተካሂዷል፡፡

ርክክቡ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር፣ የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትር፣ የጀርመን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚንስትር፣ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር እና ሌሎችም ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

ፕ/ር ሒሩት ወ/ማርያም በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት ‹‹ጀርመን ወደ ሀያ ለሚጠጉ ዓመታት የሀገራችንን የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በቴክኒክና በፋይናንስ ስትደግፍ ቆይታለች፡፡ አሁን ደግሞ የትራክተሮችና ማሽነሪዎች ድጋፍ አድርገውልናል፡፡ እነዚህን ማሽነሪዎች መጠቀም ግብርናውን ዘመናዊና ምርታማ የሚያደርጉ ባለሙያዎችንና ቴክሽያኖችን ለማፍራት ያግዛል››፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ለመደገፍም ያለውን ከፍተኛ ሚና በማስታወስ፡፡

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የተደራጁ ወርክ ሾፖች የስልጠና ቁሳቁሶች የሚጠይቅ በመሆኑ የተግባራዊ ስልጠናችን በሚፈለገው ደረጃ ተለውጧል ማለት አያስችልም ያሉት ፕ/ር ሒሩት ይህ ድጋፍ ክፍተቱን ለመሙላት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ያስረዳሉ፡፡

ከ80 በመቶ በላይ በግብርና የሚተዳደር ህዝብ ላላት ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማዘመን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትሩ ዶ/ር ገርል ሙለር ናቸው፡፡ የሀገራቸው ድጋፍም በዋናነት የኢትዮጵያን ግብርና ለመደገፍና ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡ ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በመጨረሻም የኢንስቲትዩቱን በጀርመን መንግስት የቁሳቁስ ድጋፍ የተደራጁ የስልጠኛ ክፍሎችን ተዟዙረው ጎብኝተዋል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti