ኢንስቲትዩቱ ለሶማሌ ላንድ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል ሰጠ፡፡ የሶማሌ ላንድ ኢምባሲ ለዜጎቹ በኢንስቲትዩቱ ነጻ የትምህርት እድል እንዲሰጣቸው ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መስፈርቱን ያሟሉ ተማሪዎችን ተቀብሏል፡፡

Federal TVET Institute

November 22, 2019

ከሶማሌ ላንድ ለመጡና ለከፍተኛ የትምህርት እድል የሚያበቃ ዉጤት ያላቸዉን ተማሪዎች በኢንስቲትዩቱ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀ ግብር ለማስተማር መቀበሉን ተከትሎ በዛሬው እለት የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ አካዳሚክ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብቶም ገ/እግዚአብሔር በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ስለ ተቋሙ በመማር ማስተማር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የጥናትና ምርምር፣ በቴክኖሎጂ መቅዳትና ማላመድ ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በዝርዝር ገለጻ አድርገዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በአለም አቀፍ ጥራት ያለው ትምህርት የሚሰጥ ከሌሎች ታዋቂና ስመ-ጥር ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ እንዲመደብ ለማስቻል ራእይያችን ላይ የተቀመጡ ግቦችን ለመፈጸም ዘርፉን በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል ፡፡

ይህንን ለማሳካት ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን ለጎረቤት ሀገራት ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል እንዲያኙ ከማድረግ ባሻገር ተማሪዎችም እርስ በዕርስ ባህላቸውን ፣ቋንቋቸውን ና ትውፊታቸውን ለማስተዋወቅ እድል ይፈጥርላቸዋል የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያጠናክር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠል የሬጅስትራልና አልሙናይ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ካሳዬ ጥላሁን ተማሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ ከ 12ተኛ ክፍል ያጠናቀቁ የዘመኑ መቁረጫ ነጥብ ውጤት ያላቸውና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በደረጃ 4 ተመዝነው ብቁ የሆኑ አሰልጣኞች ጋር ተቀላቅለው እንደሚማሩ ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ማጠቃለያ ውጤታቸው መሰረት በማድረግ ከ20 በላይ ባሉ ትምህርት ክፍሎች በመረጡት ዘርፍ ተመድበው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ስለሚወስዱአቸው የትምህርት አይነቶችና ፋይዳቸው፣ በሬጅስትራር ህጎች በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት ላይ ሰፋ ያለ ገለፃ አድርገዋል፡፡

የተማሪዎች ዲን ሀላፊ አቶ ወንድይራድ በሀይሉ ለሚገቡ አዲስ ተማሪዎች በ 4 ዓመት ቆይታ ጊዜአቸው ተማሪዎቹን መሰረታዊ እውቀት ሊያስጨብጧቸው የሚችሉ የትምህርት ዓይነቶች እንደሚሰጡና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ የዝግጅት ምዕራፍ እንደተወጠነ ገልጸዋል፡፡
ስለተማሪዎች ሥነ-ምግባር መመሪያና ስለተቋማችን ሥነ-ስርአት፣ ህግና ዲሲፕሊን ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል

ተማሪዎቻችንን በጥልቀት የሚያስቡና የሚያስተውሉ ለዚህም ኢንስቲትዩቱ ጠቃሚ ሃሳቦች በነጻነት የሚንሸራሸሩበትና ልቆ የተገኘው ሃሳብ ተደማጭነትን አግኝቶ የሚተገበርበት ቁልፍ ቦታ መሆኑን ተረድተው ለተቀመጠው የስነምግባር ደንብ ተገዢ እንደሚሆኑም ገልፀዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከአሁን በፊትም ለደበቡብ ሱዳን ተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል ሰጥቶ እያስተማረ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti