ኢንስቲትዩቱን ወደ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ለመቀየር የማስፋፊያ ቦታ ችግር መፈታት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የስልጠና ክፍሎችን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን ተማሪዎች መመገቢያ ክፍል ተገኝተው ተማሪዎችን አነጋግረዋል፡፡

Federal TVET Institute

November 22, 2019

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከሰሞኑ በፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት በመገኘት ወደ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ለመለወጥ ያለውን ዝግጅት እና የስራ አፈጻጸሙን ገምግመዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በሁሉም መንገድ መሻሻል ማሳየቱን በምልከታቸው እንደተገነዘቡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እምዬ ቢተው ተናግረዋል፡፡

የስልጠና ወርክሾፖች በተሻለ ሁኔታ በቁሳቁስ የተደራጁ መሆናቸው መማር ማስተማሩን በተሟላ ሁኔታ በተግባር ላይ የተደገፈ እንዲሆን እንደሚያስችለው መመልከታቸውንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱን ሪፖርት ያቀረቡት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተሻለ በሬቻ በዚህ የትምህርት ዘመን ከፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጆች ከመጡ ሰልጣኞች በተጨማሪ አራት መቶ የሚደርሱ አዲስ ተማሪዎች ከመሰናዶ ት/ቤቶች መቀበሉን ገልፀዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ትስስሩን ለማጠናር ከሀምሳ በላይ ከሚሆኑ ኢንስዱስትሪዎች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን በዚህም በአመት ሁለት ጊዜ የጋራ ፎረም እንደሚካሔድ የተናገሩ ሲሆን ሁሉም ተማሪዎች ኢንዱስትሪዎች ላይ የተግባር ልምምድ ሳይሔዱ የሚመረቁበት ሁኔታ የለም ብለዋል፡፡

ለተማሪዎች የምግብ ፍጆታ የተመደበላቸው በቀን አስራ አምስት ብር ብቻ መሆኑ ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ ባለመሆኑ አቅርቦት ላይ እንቅፋት እንደፈጠረ አቶ ተሻለ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ክሊኒክ ቢኖረውም አምቡላንስ አለመኖሩ ሌላው ችግር የፈጠረ ሁኔታ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አስገንዝበዋል፡፡

ተማሪዎች እና መምህራን የሚያፈልቋቸው የተለያዩ ቴክሎጂዎች እስከታች ድረስ ስለመውረዳቸው ምን እየተሰራ እንደሆነ የተጠየቁት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ቴክኖሎጂዎች ከተሰሩ በኋላ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች አሰልጣኞችን በማምጣት እንዴት መቅዳትና ማሸጋገር እንደሚችሉ ስልጠና እንደሚሰጥና እነሱ ሔደው ወደ ተጠቃሚው ያሸጋግራሉ ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱን ወደቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ለማሳደግ ሲካሔድ የነበረውን ተደጋጋሚ ጥያቄ እና ጥረት ያስታወሱት የተከበሩ ወ/ሮ እምዬ ቢተው "አሁን ያለበት ቦታ ገጽታው ጥሩ ቢሆንም ወደ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ሲቀየር ማስፋፊያ ቦታ ያስፈልገዋል፡፡ ይኸንንም ቀደም ብሎ ከሚመለከታው አካላት ጋር መነጋር ይገባል" ብለዋል፡፡

የተማሪዎች የምግብ አቅርቦትን በተመለከተ ጫራታውን በመፈተሸ ሌሎች የተሻሉ አቅራቢዎችን ለማግኘት ቢሰራ ብለው ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ ሠላማዊ የመማር ማስተማሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የቋሚ ኮሚቴ አባላት አሳስበዋል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti