የቴክኖሎጂ ውድድር ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ እድገት መሰረት እንደሆነ ተገለጸ፡፡

Federal TVET Institute

November 14, 2019

አሰልጣኞችን፣ ሰልጣኞችንና የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾን በክህሎታቸው በማወዳደር ለማበረታታትና ለአሸናፊዎች እውቅና መስጠት የሚያስችል የክህሎት ማስተግበሪያ ሰነድ ሰሞኑን ለዉይይት ቀርቧል፡፡

የክህሎት ውድድር በፌደራል፣ በክልል ፣በክላስተር እና በኮሌጆች ደረጃ በተመረጡ ሙያዎች በበጀት አመቱ እቅድ መሰረት ለማወዳደር ዝግጅቶችና የውድድር የማስፈጸሚያ ስልቶች ሁሉ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አያሌው ሳህሌ ተናግረዋል፡፡

ውድድሩ ለማካሄድ የሚዘጋጀው ፕሮጀክት የራሱ የሆነ የአፈጻጸም መመዘኛ መስፈርት እና የፍረጃ የነጥብ ገደቦች እንዲኖሩትም ይደረጋል፡፡

በረቂቅ ማስተግበሪያ ሰነዱ ላይ ዳኞች አመራረጥ መስፈርቶች የተካተተ ሲሆን ከየዘርፉ የተውጣጡ እውቀት ፣ ክህሎትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ሊሆኑ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የውድድሩ ተሳታፊዎች በአለምአቀፍ የክህሎት ውድድር ህግና መስፈርት መሰረት ምርጫ እንደሚደረግ ተነግሯል ፡፡

በውድድሩ ለሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን በሙሉ በውድድሩ ማጠናቀቂያ ላይ የተሳትፎ ምስካር ወረቀት የሚያገኙ ሲሆን የውድድሩ አሸናፊዎች የውጪ ሀገር ጉብኝት፣ የትምህርት እድል፣ የገንዘብና የሜዳልያ እንዲሁም ሌሎች የማበረታቻ ሽልማቶች እንደሚበረከትላቸው የፈደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጄንሲ ገልጿል፡፡

ከሁሉም ክልሎች የተዉጣጡ ቴክኒክና ሙያ አመራሮችና የፖሊቴክኒክ ሀላፊዎች የተገኙ ሲሆን በረቂቅ መመሪያው ላይም ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

ተሳታፊዎችም በሀገራችን በክህሎት ውድድር የተሰጠው ትኩረት ካለፈውው አመት በፊት አናሳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የየዘርፉ ባለሙያዎች ውድድሩን እንደ አንድ ቴክኖሎጂ አቅም ማጎልበቻ ተግባር ቆጥረው አለመስራት ይታይበታል ብለዋል፡፡

በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ያሉ ባለ ድርሻ አካላትና ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ ውድድር ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ እድገት መሰረት እንደሆነ ሊገነዘኑ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti