የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የማህበረሰቡ ችግር መፍቻ ጥናትና ምርምር ሰርተው ማቅረብ አለባቸው፡፡ (አቶ እንየው ጌትነት- የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር)

Federal TVET Institute

November 7, 2019

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ስራዎች ዙሪያ የሚያተኩር ውይይት ከድህረ-ምረቃ ተማሪዎች ጋር አካሂዷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንየው ጌትነት በውይይቱ ላይ እንደገለፁት የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የሚያቀርቧቸው የመመረቂያ ስራዎቻቸው የማህበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ መሆን ይገባቸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ወደ ዩንቨርስቲ ለማደግ በሚያደርገው ሂደት ለኢንዱስትሪዎች ግብአት የሚሆኑ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማፍለቂያ እና መመራመሪያ ለማድረግ እየተጋ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የድህረ ምረቃ ተማሪዎች በፈጠራ ውጤቶቻቸው የማህበረሰቡን ችግር መቅረፍ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይህም ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻል ለእያንዳንዱ የድህረ-ምረቃ ተማሪ በነፍስ ወከፍ 25ሺህ ብር የሚመደብ ሲሆን ትልልቅ ሀገራዊ የሆነ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ለሚሰሩ ገንዘቡ ከዚህም በላይ ሊፈቀድ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ተገልጿል፡፡

በእለቱ ተማሪዎች በርካታ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ከነዚህም ዋና ዋናዎቹ በግቢው ውስጥ ፈጣን ኢንተርኔት አለመኖር፣ የድህረ ምረቃ ስርአተ ትምህርት አለመስተካከል፣ በቤተ መጽሀፍት ውስጥ የሚገኙ ኮምፒውተሮች ቁጥር አናሳ ከመሆን ጋር ተያይዞ የሚጠበቀውን አይነት ውጤት ለማምጣት ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ከተማሪዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ኃላፊዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በግቢው ውስጥ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲኖር ከጀርመን ልማት ባንክ (KFW) በተገኘ ድጋፍ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

ባሳለፍነው ዓመት ማገባደጃ ላይ የኢንስቲትዩቱ የድህረ ምረቃ ት/ቤት የስርአተ ትምህርት ክለሳ ማድረጉን የተናገሩት አቶ እንየው በዚህ የትምህርት ዘመን ከስርዓተ ትምህርት ጋር የተያያዙ ክፍተቶች እንደሚቀረፉ አብራርተዋል፡፡ በቅርቡ በቤት መጽሀፍት ውስጥ የኮምፒውተር ግብአቶች ለሟሟላት ግዢ ሂደት ላይ እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የድህረምረቃ ት/ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ተ/ፕሮፌሰር አስማማው ተገኘ (ፒኤችዲ) በበኩላቸው የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የተማሩትን መሰረት አድርገው ወደ ተግባር ከመቀየር ይልቅ ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ገልብጦ የማምጣት አዝማሚያ እንደሚታይ ተናግረዋል።
ችግሩን ለመፍታትም ተመራማሪዎች ወደ ህብረተሰቡ ወርደው ለችግሮቻቸው መፍትሄና ተጠቃሚ የማድረግ ስራ መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti