የመንግስት ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ላይ የሚታይ ክፍተትን ለመሙላት የአስተዳደርና አገልግሎት ሪፎርሙን በአግባቡ መረዳትና መተግበር እንደሚያስፈልግ ተመላከተ ሀዋሳ፡ ግንቦት 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፌዴራል ስራና ክህሎት ሚኒስቴር በመንግስት አስተዳደርና አገልግሎት ሪፎርም ዙሪያ ለሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ሰራተኞች ስልጠና ሰጥቷል።

የመንግስት ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት ላይ የሚታይ ክፍተትን ለመሙላት የአስተዳደርና አገልግሎት ሪፎርሙን በአግባቡ መረዳትና መተግበር እንደሚያስፈልግ ተመላከተ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፌዴራል ስራና ክህሎት ሚኒስቴር በመንግስት አስተዳደርና አገልግሎት ሪፎርም ዙሪያ ለሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ሰራተኞች ስልጠና ሰጥቷል።
ስልጠናውን የሰጡት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሀብታሙ ሙሉጌታ የመንግስት አስተዳደር አገልግሎቶችን አሰራር ስርዓት ለማቀላጠፍና ለማዘመን እየተሰራ እንደሆነ ለሰልጣኞች ገልጸዋል።
እንደሀገር የሚታየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መቀረፍ የሚያስችል በተለይ ዜጎች ቀልጣፋና የዘመነ አገልግሎት የማግኘት መብታቸውን ሊያስጠብቅ የሚችል ማዕቀፍ መዘጋጀቱንም አንስተዋል።
ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር አንጻር የሪፎርሙ አስፈላጊነት በ3 ዘርፎች በክህሎት ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በአሰሪና ሰራተኛ ስርዓት ውስጥ ዜጎች ያለምንም እንግልት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን አገልግሎት በማዘመን ከሰዎች ንክኪ ነጻ በማድረግ የተገልጋይ ፍላጎትን አሟልቶ ማስተናገድ ያስችል ዘንድ እንደሆነም አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜያት ሲቪል ሰርቪሱ ይመራበት የነበረው አዋጅ ቢኖርም አሁን የተዘጋጀው ማዕቀፍ ሲቪል ሰርቫንቱ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ የሚቀጥልበት፣ ብዝሃነትንና አካታችነትን፣ ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ እንዲሰራ የሚያደርግ ስታንዳርድ የወጣለት ሰባት መመዘኛ ባለው እንዲመራ የሚያደርግ ማዕቀፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መዘጋጀቱንም አስታውሰዋል፡፡
አሁን የተዘጋጀው ማዕቀፍ የሚሰራውን ሰራተኛ ከማይሰራው ሰራተኛ ለይቶ ለመሸለምና ለማበረታታት እንዲሁም ክፍተት ያለባቸውን እያገዙ ከመሄድ አንጻር ግልጽ መመሪያ የያዘ በመሆኑ የመንግስት ሠራተኛውንም ሪፎርሙ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ሲቪል ሰርቪሱ መንግስት እንኳ ቢለዋወጥ ሳይነቃነቅ ስነ-ምግባርን በጠበቀ መንገድ ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ የበኩሉን እንዲወጣ ተደርጎ ማዕቀፉ የተዘጋጀ ስለሆነ ሲቪል ሰርቫንቱ ግልጽ የሆነ አረዳድ እንዲይዝ ሲሉ ዶክተር ሀብታሙ አስገንዝበዋል።
የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ ካሳሁን ናይክን በበኩላቸው ሪፎርሙ ኮሌጁ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ አካባቢውንና ሀገሪቱን የሚጠቅም ስራ እንዲሰራ ያስችላል ብለዋል።
አክለውም ሪፎርሙ ኮሌጁ ከመንግሥትና ከሌላ አካል በጀት ሳይጠብቅ በራሱ ገቢ አመንጭቶ በራሱ በጀት መንቀሳቀስ እንዲችልና አገልግሎት አሰጣጡ ከወረቀት አልፎ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ያደርጋልም ብለዋል።
የኮሌጁ አስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ዲን አቶ ግርማ ለገሰ ወደ ሪፎርሙ ለመግባት ያስችል ዘንድ ከኮሌጁ የተመረጡት ኮሚቴዎች ከፌደራል ጀምሮ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሲሰጣቸው መቆየቱን አንስተው በፖሊሲው ላይ የተቀመጡትን ሰባት አምዶች ጠብቆ ኮሌጁና ሰራተኛው አገልግሎት መስጠት ከቻሉ ሪፎርሙ በሲቪል ሰርቫንቱ ላይ የሚታየውን የአመለካከት ችግር መቅረፍ እንደሚችል አብራርተዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊ ሰራተኞች መካከል አቶ ተመስገን ደረጀ፣ ወ/ሮ አብነት ኬሮ እና አቶ ሺፈራው ባሳ ከቀረበው የሪፎርም ሰነድ ከዚህ ቀደም የነበሩትን የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን በማሻሻል ሰራተኛው ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያግዝ መሆኑን ግንዛቤ ማግኘታቸውን ጠቁመው በውስን የመንግስት መስሪያ ቤቶች እየተጀመረ ያለው ይህ ሪፎርም በሁሉም ላይ ከተተገበረ እንደሀገር የሚታየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መቅረፍ እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን