በኢንስቲትዩቱ በሰልጣኞች እና በመምራን ትብብር ከመቶ ሰባ በላይ ቴክኖሎጂዎች ተሰርተዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በ2011 በጀት ዓመት 92% መፈጸም ተችሏል ተባለ፡፡

Federal TVET Institute

ነሐሴ3/2011

የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት በ2011 በጀት ዓመት በአስተዳራዊና በአካዳሚያዊ ዘርፎች ላይ የነበረውን አፈጻጸም የነበሩ ጥንካሬዎችንና ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ውይይቱን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በሬቻ ሲሆኑ በመቀጠልም የዋና ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ሲሳይ ክፍሌ ዓመታዊ ሪፖርቱን አቅርበዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የስልጠና ጥራትን ለማጎልበት የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ጥቂቶቹም ለአሰልጣኞች የትምርት ደረጃ ለማሻሻል የትምህርት እድሎች /scholarship/ በማመቻቸት እንዲማሩ መደረጉ፤ የስልጠና ክፍሎች በዘመናዊ ማሰልጠኛ ቁሳቁሶች እንሟሉ መደረጉ፤ የሳተላይት ተቋማትን በቁሳቁስ የመደገፍ ስራ መሰራቱ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
የሰልጣኞች አጠቃላይ ቅበላን በተመለከተ በዋናው ግቢ እና በሳተላይት ካምፓሶች 8ሺ 9 መቶ 41 ሰልጣኞችን መቀበል የተቻለ ሲሆን በዚሁ ትምህርት ዘመን 1ሺ 450 ሰልጣኞችን በደመቀ ሁኔታ ማስመረቅ ተችሏ ተብሏል፡፡
ከአርባ አራት ኢንዱስትሪዎች ጋር የትብብር ስልጠና መስጠት ተችሏል፡፡ በዚህም ሰልጣኞቻችን ወደ ኢንዱትሪዎች በመሄድ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ የተሰራ ሲሆን የኢንዱስትሪ ቴክኒሽያኖችም በኢንስቲትዩቱ አጫጭር የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ ተቋማት እና ከተለያዩ ክልሎች ለመጡ ባለሙያዎች የእድሉ ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡
ከኢንስቲትዩቱ ተልዕኮዎች አንዱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ሽግግር ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ በዓመቱ ከመቶ ሰባ በላይ ቴክኖሎጂዎች ተሰርተዋል፡፡ በዝርዝር ሲታይ በዋናው ግቢ ባሉ የውጭአገር መምህራን 2፣ በሀገር ውስጥ መምህራን 12፣ በሳተላይት መምህራን 13፣ በተመራቂዎች እና በመምራን ትብብር 176 ቴክኖሎጂዎች የተሰሩ ሲሆን የተመረጡ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ዓለምአቀፍ ግንኙነትን ለማጠናከር በሰራው ስራ 71 ለሚሆኑ የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች የትምህርት እድል በመስጠት እያስተማረ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ሌላው በ2011 ዓ/ም የተከናወነ ዋና ጉዳይ በአገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪ የሆነውን የቴክኒክና ሙያ የቴክኖሎጂ የክህሎት የጥናትና ምርምር ውድድርና ኤግዚቢሽን ተካሔዶ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡
ኢንስቲትዩቱን ወደዩኒቨርሲቲ ለማሳደግ የሚያስችል ምክረሀሳብ ቀርቦ በመንግስት ጥናት እየተደረገበት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
እነዚህ ጥንካሬዎች ቢኖሩም የበለጠ ውጤታማ ስራዎች እንዳይሰሩ ያደረጉ እንቅፋቶችም አልጠፉም፤ ጥቂቶችም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የክህሎትና የአመለካከት ችግር በተለይም IFIS ላይ፣ የሰውሀይል እጥረት፣ የግዥ መዘግየት ችግር፣ የተማሪዎች የነፍስ ወከፍ ገቢ እና የገበያ ሁኔታው አለመመጣጠን የተማሪዎች ምግብ አቅራቢዎች ማቆራረጥና ማቋረጥ አጋጥሞ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ 
በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ በበጀት ዓመቱ 92% መፈጸም ተችሏል ተብሏል፡፡

 


Don't forget to visit our other Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti