የኢፌደሪ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኢንስቲትዩት በማስተርስ ዲግሪና በመጀመሪያ ዲግሪያ ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 454 ተማሪዎችን አስመረቀ።

Federal TVET Institute

ሀምሌ 6/ 2011

ኢንስቲትዩቱ በዕለቱ 218 ሴትና 1ሺህ 236 ወንድ ተማሪዎችን በማስተርስ ዲግሪና በመጀመሪያ ዲግሪ አሰልጥኖ አስመርቋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ኢትዮጵያን ወደላቀ ሁለንተናዊ እድገት ለማድረስ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ ያለ ኢንስቲትዩት መሆኑን ገልጸው፤ ወጣቱ የማህበረሰቡን ችግር የመፍታት አቅም እንዲኖረው፤ ስራ ፈላጊ ሳይሆን ስራ ፈጣሪና በስነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን ያሳሰቡት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በሬቻ ናቸው።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንትና የኢንስቲትዩቱ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ለሚ ጉደታ በበኩላቸው እየተመዘገበ ያለው አገራዊ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረውና በዘላቂነት የዜጎችን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ የሚያደርጉ የሰለጠኑ፤ ብቃትና ተገቢ አመለካከት ያላቸውን የሰው ሃይል በሚፈለገው ብዛትና ጥራት ማፍራት ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ዶክተር ለሚ አክለውም ተማሪዎች አስፈላጊና ችግር ፈቺ የሆኑ ግብአቶችን በመፍጠር አገራቸው የምትጠብቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ችግር ፈቺ የሆነ ፈጠራቸውን ይዘው የቀረቡት የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት የማስተርስ ተማሪ አቶ በውቀቱ ዘላለም የአየር ንብረት የማይበክልየግሪስ ማሽንና ግሪስ አምርተው ይዘው ቀርበዋል።

በዚህም አገሪቷ ከውጭ የምታስገባውን ምርት ለመቀነስና የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት ባሻገር ከስኳር በሚገኝ ተረፈ ምርት የሚዘጋጅ በመሆኑም ዋጋው አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው ችግር ፈቺ ምርት ይዘው የቀረቡት በማኑፋክቸሪንግ የማስተርስ ዲግሪ ተማሪ አቶ ነገሰ ቀኒዓለም  በበኩላቸው የሻማ ማምረቻ ይዘው ቀርበዋል።

ይህም የሻማ ምርትን በአገራችን በብዛት በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብና ለበርካታ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቲክስታይል ቴክኖሎጅ የትምህርት ክፍል ተማሪ የሆነችውና የላቀ የትምህርት ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪ ታደሉ ጌቱ  በበኩሏ በተማረችበት የትምህርት ዘርፍ የሚጠበቀባትን ለማበርከትና ስራ ጠባቂ ሳትሆን ስራ ፈጣሪ በመሆን ልትሰራ ማሰቧን ገልጻለች።

ኢንስቲትዩቱ በደንብ ቁጥር 245/2003 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ከመጀመሪያ ዲግሪ በተጨማሪ በሁለተኛ ዲግሪ ስልጠና በመስጠት ሲያስመርቅ ይህ ለአምስተኛ ጊዜው ነው።

(ፎቶ- ከኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት)

 


Don't forget to visit our Facebook page for other News and Updates!
https://www.facebook.com/tveti